ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በኮሎምብያ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ ጨዋታውን ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በኮሎምብያ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው 11ኛው የፊፋ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ ጨዋታውን ዛሬ በአዲስ አበባ ያደርጋል።

ቡድኑ ባሳለፍነው ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም ከሞሮኮ አቻው ጋር በአልጀዲዳ ከተማ ኤላብዲ ስታዲየም ያደረገውን የመጀመሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

በዛሬው ዕለት ከቀኑ በ9 ሰዓት የመልስ ጨዋታውን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያከናውናል።

ብሔራዊ ቡድኑ ለማሸነፍና ውጤቱን ለመቀልበስ ከሁለት በላይ ጎሎችን ማስቆጠር ይጠበቅበታል።

የቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል 22 ተጨዋቾችን በመያዝ ልምምዱን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲያደርግ ቆይቷል።

በዛሬው ጨዋታ ኳስን መሠረት ያደረገና በማጥቃት ላይ ትኩረት ያደረገ ጨዋታ ለመጫወት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን፤ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻለ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በፊፋ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዛሬው የመጨረሻ የደርሶ መልስ ጨዋታ የደረሰው ኢኳቶሪያል ጊኒና ማሊን በማሸነፍ መሆኑ የሚታወስ ነው።

ኮሎምቢያ በምታስተናግደው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ 24 ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን አፍሪካ አራት ሀገራትን የማሳተፍ ኮታ በፊፋ ተሰጥቷታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም