ኢትዮጵያ ለጅቡቲ የምታቀርበው የንጹህ መጠጥ ውሃ መጠን በቀን ወደ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ሊያድግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለጅቡቲ የምታቀርበው የንጹህ መጠጥ ውሃ መጠን በቀን ወደ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ሊያድግ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለጅቡቲ በቀን የምታቀርበው 20 ሺህ ሜትርኪዩብ የንጹህ መጠጥ ውሃ መጠን ወደ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ሊያድግ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮ-ጅቡቲ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመሳሳይ ማንነት የሚጋሩ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦችን በኢኮኖሚ የሚያስተሳስር የቀጣናዊ የጋራ ልማት ማሳያ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር ዘለል የንጹህ ውሃ ፕሮጀክት በሁለቱ ሀገራት የውሃ አቅርቦት ስምምነት መሰረት ከስድስት ዓመታት በፊት ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
በሶማሌ ክልል በተቆፈሩ 28 የከርሰ ምድር ጉድጓዶች አማካኝነት የሚወጣው ውሃ ከሺንሌ-ሚሎ-ሐረዋ- አዲጋላ-ለአስራት-አይሻ-ደወሌ በመጨረሻም ጅቡቲ ከተማ ለመድረስ 258 ኪሎሜትር ርዝመት አለው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እና በድሬዳዋ የጅቡቲ ቆንስላ ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሙሳ ሃጂ ጀማል የተመሩ የሁለቱ ሀገራት ልዑካን በሶማሌ ክልል አዲጋላ እና አካባቢው ተዘዋውረው የፕሮጀክቱን እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አሁናዊ ሁኔታና የማሻሻያ ስራዎችን በመመልከትም ከማሻሻያ ስራዎች አፈጻጸም እና ከውሃ መስመሩ ጋር የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች በአጭር ጊዜ እንዲፈቱ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ የኢትዮ-ጅቡቲ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመሳሳይ ማንነት የሚጋሩ የሁለቱ ሀገራትን ህዝቦች በኢኮኖሚ የሚያስተሳስር የቀጣናዊ የጋራ ዕድገትና ልማት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልልም ሆነ በተቀረው የኢትዮጵያ አካባቢ የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት እንዳለ ያነሱት ሚኒስትሩ፣ ፕሮጀክቱ ዕውን የሆነው ኢትዮጵያ የጋራ ችግሮችና ዕድሎችን ለመጋራት ካላት ፍላጎትና ቁርጠኝነት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ጅቡቲ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች እየተሳሰሩ መምጣታቸው ለቀጣናዊ ትስሰር አብነት መሆኑን ጠቅሰው፣ የውሃ ፕሮጀክቱም የዚሁ ሁነኛ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ የንጹህ መጠጥ ውህ ፕሮጀክት ወደ ጅቡቲ ከሚሄደው የውሃ መጠን ውስጥ በሚያልፍባቸው ከተሞች እስከ 5 ሺህ ሜትር ኪዩብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መወሰኑንም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት ከጉድጓዶች ውሃ ለመሳብ በነዳጅ በመጠቀም በቀን እስከ 20 ሺህ ሜትርኪዩብ ያመነጭ እንደነበር ገልጸው፣ በነዳጅ የነበረውን ወደ አሌክትሪክ በመቀየር በቀን 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ እንዲያመነጭ ይደረጋል ብለዋል።
በዚህም የማሻሻያ ተግባራት በአንድ ወር ውስጥ ተጠናቀው በቀን የታለመለትን መጠን እንዲያመነጭና በጅቡቲ ያለውን የውህ ፍላጎት እንዲሸፍን ይደረጋል ነው ያሉት።
በድሬደዋ የጅቡቲ ቆንስላ ዳይሬከተር ጄኔራል አምባሳደር ሙሳ ሃጂ ጀማል በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጅቡቲ በባቡር፣ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ ኅይል፣ በውሃና በሌሎች መሰረተ ልማቶች እየተሳሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመበልጸግ ያላቸውን ዕድል የሚያሰፋ በመሆኑ በቀጣይም ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ይበልጥ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በደም የተሳሰሩ አንድ በመሆናቸው የውሃ ፕሮጀክቱም የወንድማማች ህዝቦችን በጋራ የሚጠቀሙበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ዜጎች ሁለተኛ ሀገራቸው መሆኗን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃን ጨምሮ በመሰረተ ልማት በጋራ ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነትና ፍላጎት አድንቀዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለጅቡቲ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከአፈጻጸም ጋር የሚስተዋሉ ከፍተቶችን ጋራ በመቅረፍ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።