ቀጥታ፡

የጥምቀትን በዓል የአብሮነትና የአንድነት እሴቶችን ባጎለበተ መልኩ አክብረናል---በድሬዳዋ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች 

ድሬዳዋ ጥር 11/2016(ኢዜአ)፦የጥምቀት በዓልን የአብሮነትና የአንድነት እሴቶችን ባጎለበተ መልኩ ማክበራቸውን የድሬዳዋ ከተማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት እምነት ተከታዮች ገለጹ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የእምነቱ ተከታዮች እንደተናገሩት የአደባባይ በዓል የሆነውን የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ እሴቶች የሆኑትን አብሮነትና አንድነት ባስጠበቀ መልኩ አክብረውታል።

በትናንቱ የከተራ እና በዛሬው የጥምቀት በዓል ታቦታት በሚያልፉባቸው ጎዳናዎች የሌሎች እምነት ተከታዮች ያደረጉላቸው የዓይነትና የሞራል ድጋፍ አበረታች መሆኑንም አቶ ዓለማየሁ አድማሱና አቶ መሥፍን ንጉሤ የተባሉ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

''በተለይ በበዓሉ ላይ የእምነቱ ተከታይ ያልሆኑ ወንድምና እህቶች ለበዓሉ ድምቀት የድርሻቸውን በመወጣት የድሬዳዋን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ፍቅር በማንፀባረቅ በዓሉን አድምቀዋል'' ብለዋል አቶ ዓለማየሁ።

በዓሉን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ በፍቅር ከማክበር በላይ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ለመደገፍ መዘጋጀቷን የገለጸችው  ደግሞ ወጣት መድኃኒት መላኩ የተባለች የከተማው ነዋሪ ናት።

የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለ ሚካኤል በበኩላቸው ጽህፈት ቤቱ  በድሬዳዋ አስተዳደር ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለበዓሉ አክባሪዎች ማስተዋወቁን ገልጸዋል።

በአስተዳደሩ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የሚጎበኙ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፣ የጥምቀት በዓልን በመጠቀም ይሄን ለማጠናከርና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም