የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማስፈን ተግተን እንሰራለን -የፀጥታ አካላት - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማስፈን ተግተን እንሰራለን -የፀጥታ አካላት
ደሴ /ደብረ ብርሃን ፤ ጥር 11/2016 (ኢዜአ)፡- የአማራ ክልልን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ተግተው እንደሚሰሩ የምስራቅ አማራ የፀጥታ አካላት ገለፁ።
በደሴ እና ደብረ ብርሃን ከተሞች ለአንድ ሳምንት ለፀጥታ አካላት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የፖሊስ አባል ኮማንደር ደጀን ወዳጅ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የተሰጠው ስልጠና የክልሉን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ተረድቶ የጋራ አመለካከት ለመያዝ እና ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሚያግዝ ነው።
የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ አባል ኮማንደር የሺወርቅ ላቀው በበኩላቸው፤ ስልጠናው የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
በስልጠናው ወቅታዊ ሁኔታን በትክክል ለመረዳት እንዳስቻላቸው ጠቁመው፣ በቀጣይ ለክልሉ ሰላም መጠበቅ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ስልጠናው ህዝብን በማሳተፍ ሰላምን ለማስፈን ሁለተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው ያሉት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሚሊሻ ጽህፈት ቤት አባል ዋና ሳጅን መሃመድ ደሳለኝ ናቸው።
በጦርነት አስከፊነት፣ በሰላም ጥቅም እና ችግርን ተቋቁሞ ሰላም መፍጠር ላይ አተኩሮ ስልጠናው መሰጠቱን ገልጸው፤ ክፍተትን በማረም ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና አንድነት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር እሸቱ የሱፍ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በክልሉ የተገኘውን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ከህዝብ ጋር ተከታታይ ውይይት ተደርጓል።
ህብረተሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላምና ልማት እንዲያጠናክር ለፀጥታ አባላት የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ገልፀዋል።
የስልጠናው ዓላማ ሁሉም የፀጥታ አካሉ የጋራ አመለካከት እንዲይዝ ከማድረግ ባለፈ ለህብረተሰቡ ደህንነት ሲባል የጥፋት ሀይሎችን የመመከትና ህግ የማስከበር ሥራውን እንዲያጠናክር ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል በበኩላቸው ፤የአገር መከላከያ ሠራዊት ከሌሎች ፀጥታ አባላትና ህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ህግ እያስከበረ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በአካባቢው ሰላም መስፈኑን ጠቁመው፣ ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግና የአገርን እድገት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።
በአማራ ክልል ከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አህመዲን መሀመድ በበኩላቸው እንዳሉት፤ "ለአገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የፀጥታ ሀይሉ በጥፋት ተግባር የተሰማሩ ሃይሎችን መታገል አለበት።
ስልጠናው በእውቀትና በአመለካከት ቆራጥ የሆነ የፀጥታ አባልና አመራር ለመፍጠር የተዘጋጀና የተሳካ መሆኑንም ገልፀዋል።
ሰልጣኞች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ግንዛቤ ወደመጡበት አካባቢ ሲመለሱ ጽንፈኝነትና ጎጠኝነትን በመታገል ለዘላቂ ሰላም መስፈን ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የኮማንዶና አየር ወለድ ዋና አዛዥ እና የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በበኩላቸው፣ የህዝቡን ሰላምን ለማረጋገጥ አመራሩና የፀጥታ ዘርፉን በመቀናጀት መስራት የሚያስችል ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።
ሰልጣኞች የተሰጣቸውን የመንግስትና የህዝብ አደራ በቁርጠኝነት እንዲወጡም አስገንዝበዋል።