ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2016 (ኢዜአ)፦ የጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ 

የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በላከዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ ካስመዘገበቻቸው ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገራችን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሰላማዊ ሁኔታ በድምቀት ተከብሮ ተጠናቋል ብሏል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የየአድባራቱ አስተዳዳሪዎች፣ የበዓሉ አስተባባሪዎች እና የበዓሉ ታዳሚዎች በየደረጃው ከሚገኙት የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በመሥራታቸው በዓሉ ያለምንም ፀጥታ ችግር በሰላም ተከብሯል ሲል የጋራ ግብረ-ኃይሉ በመግለጫው አመላክቷል።

መግለጫው አያይዞም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ባዘጋጀው የፀጥታ ዕቅድ እየተመራ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት በማስቀደም ከዋዜማ ጀምሮ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥበቃና እጀባ ተግባራትን በማከናወን በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ኃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡ የፀጥታ ተቋማት አመራሮችና አባላት ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል።

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ አክሎም የሃይማኖት አባቶች፣ የየአድባራቱ አስተዳዳሪዎች፣ የበዓሉ አስተባባሪዎች፣ ምዕመናን እና የበዓሉ ታዳሚዎች በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ላደረጉት ትብብርና ድጋፍ በመግለጫው ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል።

በመጨረሻም በነገው ዕለት የሚከበረው የቃና ዘገሊላ በዓል እንደዛሬው ሁሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሕብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ በመግለጫው ጥሪ አቅርቦ ኅብረተሰቡ እስከአሁን ላደረገው ቀና ትብብርም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል።

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል

ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም