ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓት እጅግ ማራኪ ነው - በበዓሉ ላይ የታደሙ ቱሪስቶች

አርባ ምንጭ፤ ጥር 11/2016 (ኢዜአ)፦ ማራኪ በሆነው የጥምቀት በዓል ላይ ለመታደም በመቻላቸው መደሰታቸውን ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ቱሪስቶች ገለጹ።

በአርባ ምንጭ ከተማ የጥምቀት በዓል ላይ የተገኙት ቱሪስቶች በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል እጅግ ማራኪ መሆኑን ገልጸው፣ ለሌሎች እንደሚያስተዋውቁት ገልጸዋል።

ከፈረንሳይ ሀገር እንደመጡና በበዓሉ ላይ ሲታደሙ የመጀመሪያቸው እንደሆነ የተናገሩት ሚስተር ማክስም ፍሬድሪች የኢትዮጵያን ጥምቀት በዓል ለመታደም ዕድሉን በማግኘታቸው መደሰታቸውን ጠቁመዋል።

በበዓሉ ላይ የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን የሚያሳዩት ሃይማኖታዊ ስርዓት ለዓይን ማራኪ መሆኑን ገልጸው፤ እዚህ በዓል ላይ መታደም በመቻሌ ደስተኛና ዕድለኛ ነኝ ብለዋል።

አንድ አይነትና ማራኪ አልባሳትን ለብሰው በአንድነት ሲዘምሩና ሲያሸበሽቡ ማየት እጅግ ደስ ይላል፤ ይህም የኢትዮጵያን የጥምቀት በዓል ለየት ያደርገዋል በማለት ነው የገለጹት።

ሚስተር ፍሬድሪክ እንደገለጹት፤ ስለጥምቀት በዓል የሰሙትን ሃይማኖታዊ ስርዓትና ባህላዊ እሴት እዚህ በተግባር ለማየት በመቻላቸው መደነቃቸውን በመግለጽ።

ወደ ሀገሬ ስመለስ ወዳጅ ዘመዶቼ በቀጣይ በበዓሉ ላይ እንዲታደሙ አደርጋለሁ ያሉት ሚስተር ፍሬድሪክ፤ የኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አከባበር የደመቀና የተለየን መስህብ የዓለም ህዝብ መመልከት እንዳለበት ነው ያመለከቱት።


 

የጥምቀት በዓል አከባበርን ለመመልከት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን የገለጸችው አሜሪካዊቷ ቻርኔል ሮበርት፤ ኢትዮጵያውያን በባህላዊ አልባሳት በአንድነት ደምቀው በሚያከብሩት በዓል ላይ በመገኘቴ ደስ ብሎኛል ብላለች።

በዓሉን ለመታደም ከመጣችበት ጊዜ ጀምሮ ቱሪስቶች በነፃነት ተንቀሳቅሰው የበዓሉን ድባብ ለመመልከት የቻሉበት ሁኔታ እንደነበረም ተናግራለች።

ክብረ በዓሉ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት የተመዘገበ በመሆኑ በጋራ ልናከብረውና ልንከባከበው ይገባል ነው ያለችው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም