በተለያዩ አገራት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ለመቄዶንያ የማዕድ ማጋራትና የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ አገራት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ለመቄዶንያ የማዕድ ማጋራትና የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2016 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት የወከሉ አምባሳደሮች ለመቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የማዕድ ማጋራትና የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።
አምባሳደሮቹ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ መቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የተገኙት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን፤ የማዕከሉ አገልግሎት በአርዓያነት የሚወሰድ መልካም ተግባር በመሆኑ ሁላችንም ማገዝ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የተለያዩ አገራት ለዜጎች ድጋፍ የሚያደርጉበት የማኅበራዊ ዋስትና የአሠራር ሥርዓት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን መደገፍ ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም በዛሬው ዕለት በተለያዩ አገራት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ለመቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል አብሮነትና ድጋፋቸውን አሳይተዋል ብለዋል።
አምባሳደሮቹ በእለቱ በጉብኝታቸው የማዕድ ማጋራትና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፤ በቀጣይ የተጠናከረ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር አብዲ ያሲን፤ ከዲፕሎማሲ ሥራችን ባለፈ በሀገራችን ለበጎ ተግባራት እገዛና ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
"አቅመ ደካሞችን ማገዝ የእኛ ኃላፊነት ነው፤ በዚህ በኩል አስፈላጊውን ኃብት በማሰባሰብ የበኩላችንን እወጣለን" ያሉት ደግሞ በፈረንሳይ የኢፌዴሪ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ ናቸው።
የመቄዶንያ አረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የክብር ዶክተር ቢንያም በለጠ፤ ለማዕከሉ የሚደረጉ ድጋፎች ቀጣይነት ያላቸው እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
በተለይም ማዕከሉ የሚያስገነባቸው ሕንፃዎች በርካታ ወጪ የሚጠይቁ በመሆናቸው በውጭ የሚኖሩ ወገኖች በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
አምባሳደሮቹ በማዕከሉ ጉብኝት በማድረግ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ "የአገራችን ብቻ ሳይሆን የመቄዶንያም አምባሳደር እንድትሆኑ እንፈልጋለን" ብለዋል።
የመቄዶንያ አረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በአሁኑ ወቅት ከ7 ሺህ 500 በላይ አቅመ ደካሞችን በአዲስ አበባ እና በክልል 26 ከተሞች እየረዳ መሆኑ ይታወቃል።