ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል የሰላም፣ የፍቅርና የትህትና መገለጫ የዘወትር እሴታችን ሆኖ ሊቀጥል ይገባል- ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ 

አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2016 (ኢዜአ)፡- የጥምቀት በዓል የሰላም፣ የፍቅርና የትህትና መገለጫ የዘወትር እሴታችን ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ተናገሩ።

በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በድምቀት ተከብሯል። 

በዓሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ፣ የቤተክርስቲያኗ ካህናትና ምዕመናን በተገኙበት በአዲስ አበባ ልደታ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል ነው የተከበረው።


 

የቤተ ክርስቲያኗ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ በቅዳሴ፣ በዝማሬና በባህረ-ጥምቀት ሥነ-ሥርዓት መከበሩን ገልጸዋል።

የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ ትህትናንና ፍቅርን ያስተማረበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የበዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የትህትና መገለጫዎች የዘወትር እሴቶቻችን ሆነው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።


 

በቤተ ክርስቲያኗ የጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ አባ ተሾመ ፍቅሬ እና ወይዘሮ አዜብ ታደሰ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀት በዓል ያሳየውን ትህትና እያንዳንዳችን ዝቅ ብለን እንድናገለግልና እንድንተባበር የሚያደርገን ነው ብለዋል።


 

በዚህም ሁላችንም አስተምህሮቱን በመተግበር ጥላቻን በማስወገድ ለአንድነትና ለዕርቀ-ሰላም መትጋት ይኖርብናል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም