ቀጥታ፡

ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶችን በመጠበቅ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መቆም አለብን - የጥምቀት በዓል ታዳሚዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን እምቅ ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች በመጠበቅ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መቆም አለብን ሲሉ የጥምቀት በዓል ታዳሚዎች ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ 16 የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶችን ያስመዘገበች መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የጥምቀት በዓልም በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።

የጥምቀት በዓል በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን፤ በተለይም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ ሥፍራ የሚሰጠው በዓል ነው።

በአዲስ አበባ ጃንሜዳም የዘንድሮው የጥምቀት በዓል የሃይማኖት አባቶች፣ ምዕመናንና የተለያዩ ሀገራት ቱሪስቶች በተገኙበት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው አቶ ምንተስኖት ታምሩ፤ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እሴቱም ባለፈ በማኅበራዊ እሴትነቱ የእርስ በርስ ግንኙነትን የሚያጠናክር ትልቅ ኃብት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጥምቀት በዓል አከባበር በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበ የሀገርም የዓለምም ኃብት በመሆኑ እሴቱ ተጠብቆ እንዲዘልቅ የሁላችንም አደራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ እምቅ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች የአብሮነታችን ማጠናከሪያና የአንድነታችን ማሳያ በመሆናቸው በጋራ ልንጠብቃቸው ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የበዓሉ ታዳሚ አቶ ወንዱ ተሾመ ናቸው።

የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ የሚታሰበውን እድገትና ልማት ለማምጣት መሥራት አለብን ነው ያሉት።

በጃንሜዳ ጥምቀትን ሲያከብሩ ያገኘናቸው ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ አቶ ንጉሴ ይባስ፤ የሰላም ጉዳይ የጋራ ኃላፊነት እንጂ በአንድ አካል ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ሁላችንም የሰላማችን አምባሳደር ሆነን እንስራ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም