ቀጥታ፡

ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንን ለህዝቦች ሰላም ፍቅርና አብሮነት ልናውላቸው ይገባል 

ጎንደር ፤ጥር 11/2016 (ኢዜአ፡- ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንን ለህዝቦች ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት ልናውላቸው ይገባል ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ዮሃንስ ተናገሩ፡፡

በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል በፋሲለደስ ጥምቀተ ባህር የእምነቱ ተከታዮችና እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሃንስ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የቤተ ክርስቲያን ዘመን ተሻጋሪ ሃይማኖታዊ ስርዓቶችና እሴቶች ሰላምን፣ ፍቅርንና ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል፡፡


 

በዓሉን ስናከብር ስለ ሰላም፣ ስለ ህዝቦች አንድነትና አብሮነት በጥልቀት በማሰብና በማስተማር ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱን በዕለት ተዕለት ህይወታችን ልንተገብረው ይገባል ሲሉ ተናግርዋል፡፡ 

የጥምቀት በዓል ክርስቶሰ በፍጹም ትህትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዞ በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሃንስ እጅ የተጠመቀበትን ዕለት የሚታሰብበት አብይ በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የበዓሉ መከበርም የአብሮነት እሴትንና አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል።


 

የመንበረ መንግስት መድሃኒአለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ አዲስ በበኩላቸው፤ ሰላም የሰው ልጆች ሁሉ የፍቅር መገለጫ በመሆኑ ለሰላም አጥብቀን እንፀልይ ብለዋል፡፡

ህዝበ ክርስቲያኑ የክርስቶስን አርዓያነትና ትህትና በመከተል በሀገራችን ሰላም እንዲወርድ በመጾምና በመፀለይ በአብሮነትና በፍቅር የእግዚአብሄርን መንገድ ልንከተል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከግጭት ድባብ ወጥተን የጥምቀት በዓሉን በአደባባይ በሰላም ልናከብር በመብቃታችን ደስታ ተሰምቶኛል ያሉት ደግሞ የበዓሉ ታዳሚ አባ ተሻገር አሳዬ ናቸው፡፡

ሰላም ከሌለ የሰው ልጅ በህይወት መኖርም ሆነ ለዓለም ያበረከታቸውን ስልጣኔና ጥበቦች ለትውልድ ማሻገር እንደማይቻል ጠቅሰው፤ ለሰላም አጥብቆ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ 

በዓሉን የእምነቱ ተከታዮችን ጨምሮ የውጪ ሀገር ቱሪስቶችና እንግዶችም የታደሙት ሲሆን ታቦታቱ ከጥምቀተ ባህሩ ወደ መንበረ መቀመጫቸው ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ በክብር ታጅበው ተሸኝተዋል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም