ቀጥታ፡

የከተራና ጥምቀት በዓላት የኢትዮጵያ ድንቅ ባህልና የቱሪዝም ሀብት የያዘች ሀገር መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው - የውጭ ሀገር ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2016(ኢዜአ)፦ የከተራና ጥምቀት በዓላት ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቆየ ባህልና የቱሪዝም ሀብት የያዘች ሀገር መሆኗን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ገለጹ።

ቱሪስቶች የሰው ዘር መገኛ የሆነችውን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

የ2016 የከተራ በዓል በጃንሜዳ ዛሬ ተከብሯል።

የከተራና ጥምቀት በዓል በአደባባይ የሚከበሩና በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ከሚታደሙባቸው በዓላት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸው ይታወቃል።

ከአሜሪካ የመጣው አንድሪው አሊስ የከተራና ጥምቀት በዓል ላይ ሲታደም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ገልጾ በዓሉ ላይ መታደሙ ልዩ ደስታ እንደፈጠረለት ተናግሯል።

ኢትዮጵያ በባህል የበለፀገች መሆኗን መመልከቱ እንዳስደነቀውም አመልክቷል።

የከተራና ጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ስታደም ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው ያለው ካሜሩናዊው ሲልቫ አቻኮ በበኩሉ በዓሉ ልዩና የአንድነትን መልዕክት የሚያስተላልፍ በቀለም ያሸበረቀ ደማቅ ስነ-ስርዓት መሆኑን ገልጿል።

ከስፔን የመጡት ሱራ ስፓንዴሮና ፍራንሴስኮ ትሬዶ በበኩላቸው በበዓሉ ላይ መታደማቸው ልዩ ደስታን እንደፈጠረላቸው ገልጸው የሕዝቡን እንግዳ ተቀባይነት አድንቀዋል።


 

ካሜሮናዊው ሲልቫ አቻኮ ኢትዮጵያውያን በአደባባይ ተሰብስበው በዓላትን የሚያከብሩበት መንገድ ሳቢ በመሆኑ ሌሎች ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ያላትን ታሪክና ባህል እንዲጎበኙ ጥሪውን አቅርቧል።

አሜሪካዊው አንድሪው አሊስ እና ስፔናዊው ፍራንሴስኮ ትሬዶ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ጥምቀትን ጨምሮ ሌሎች ደማቅ በዓላትን በኢትዮጵያ በመምጣት እንዲያከብሩ እናበረታታለን ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም