የከተራና ጥምቀት በዓላት ከሃይማኖታዊ ትውፊታቸው ባሻገር የአገርን ገፅታ ለመገንባት ጉልህ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
የከተራና ጥምቀት በዓላት ከሃይማኖታዊ ትውፊታቸው ባሻገር የአገርን ገፅታ ለመገንባት ጉልህ ሚና አላቸው
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2016 (ኢዜአ)፦ የከተራና ጥምቀት በዓላት ከሃይማኖታዊ ትውፊታቸው ባሻገር የአገርን ገፅታ ለመገንባት ጉልህ ሚና እንዳላቸው የበዓሉ ታዳሚዎች ገለፁ።
የከተራና ጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፋ ለማድረግ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል።
የክርስትና እምነት ተከታዮች በተለያዩ አልባሳት ደምቀው የከተራ በዓልን ለማክበር በጃንሜዳ ታድመዋል።
የጥምቀት በዓልን ለመታደም በርካታ የውጭ አገር ዜጎች በየአመቱ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ።
በከተራ ላይ የታደሙ በተለያዩ የባህል አልባሳት ደምቀው በጃንሜዳ የተገኙ የእምነቱ ተከታዮች፤ ከተራና ጥምቀት ከሃይማኖታዊ ትውፊትነታቸው ባለፈ የአገርን ገፅታ ለመገንባት ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል።
ወጣት የሺመቤት ንጉሴና እየሩሳሌም አዱኛ የጥምቀት በዓል ከመድረሱ ከወራት በፊት በእለቱ ስለሚለብሱት አልባሳት ዝግጅት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጋራ በመሆን ተመሳሳይ ልብስ መልበስ እየተለመደ የመጣ መሆኑ ለበዓሉ ከፍተኛ ድምቀት እየሆነ መጥቷል ነው የሚሉት።
ጥምቀትን ሁሉም ሰው ባለው አቅም ልክ ተውቦና ደምቆ መታየት እንደሚፈልግ ገልፀው፤ ይህም የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ የሚፈጥረው እድል ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የጥምቀት በዓል በአለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ በተለይም ወጣቱ ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲቆይ የራሱን ድርሻ ማበርከት ይገባዋል ብለዋል።
ቤተልሔም ተስፋዬ የበኩሏ በከተራና ጥምቀት በዓላትን ለመታደም የተለያዩ አገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ተከትሎ አልባሳቱ የአገርን ገፅታ ለመገንባትና ባህልን ለማስተዋወቅ ያስችላል ብላለች።
ሌላው የበዓሉ ታዳሚ አቶ አለልኝ ውበቱ ከተራና ጥምቀት በጉጉት የሚጠበቁ በዓላት ናቸው ብለዋል።
ምዕመኑ የክትልብሱን ለብሶ አምሮና ደምቆ ለመታየት የሚያደርገው ጥረትም ቀኑን ምን ያህል በጉጉት እንደሚጠብቀው ያሳያል ነው ያሉት።
ብሄር ብሄረሰቦች ባህላቸውን ለማስተዋወቅ የሚያደርጉት ትዕይንትም የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስብ እንደሆነም አንስተዋል።
ጥምቀት የኢትዮጵያ ባህል ለአለም እንዲተዋወቅ ትልቅ አስተዋጾኦ ያለው በመሆኑ ሁሉም ዜጋ አገሩን ለማስተዋወቅ ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።