የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከጣሊያን ዜና አገልግሎት (ANSA) ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከጣሊያን ዜና አገልግሎት (ANSA) ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የጣሊያን ዜና አገልግሎት ( ANSA) በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡
በበየነ መረብ የተከናወነውን የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እና የጣሊያን ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቴፋኖ ዴ አሌሳንድሪ ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ የመግባቢያ ስምምነቱ ሁለቱ የዜና አገልግሎቶች ተልዕኳቸውን ለማሳካት የሚያስችል የትብብር ስራ እንዲሰሩ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
ኢዜአ ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና አገራዊ ገጽታ መገንባት በአዋጅ የተሰጡት አበይት ተልዕኮዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢዜአ በርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶችን በመዘገብ የሚታወቅ የዜና ተቋም መሆኑን ጠቁመው ከዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ጋር በትብብር መስራቱ እንደ ሀገር የላቀ አስተዋጽኦ ለማበርከት ያስችለዋል ብለዋል።
እንዲህ አይነት ስምምነቶች ኢትዮጵያ ያላትን እውነታ፣ እያከናወነች ያለችውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለሌሎች አገራት ለማሳወቅ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ያመለከቱት።
ስምምነቱ የኢትዮጵያና የጣልያንን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚመለከቱ መረጃዎችንና ዜናዎችን ለመለዋወጥ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ኢዜአ ከዚህ ቀደም ከበርካታ ዓለም አቀፍ የዜና አገልግሎት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን ጠቁመው እንዲህ ያሉ ስምምነቶች ተቋማቱ በሚያዘጋጇቸው መድረኮች ላይ በመገኘት የኢትዮጵያን ሀቆች ለማሳወቅ እንደሚረዳም ገልጸዋል።
ለአብነትም በቅርቡ በቻይና ጉዋንዡ ግዛት ተደርጎ በነበረው የዓለም የዜና አገልግሎቶች ፎረም ኢዜአ በዢንዋ ጋባዥነት ተሳትፎ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም ማንጸባረቁን በማስታወስ።
ስምምነቱ የጣልያን ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚረዳም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፕያዊኑ አቆጣጠር ጥር 1 2024 ቀን ጀምሮ የብሪክስ አባልነትን በይፋ መቀላቀሏን አስታውሰው ይህን ተከትሎም ኢዜአ የብሪክስ ሚዲያ ፎረም የስራ አስፈጻሚ አባል እንዲሆን ግብዣ እንደቀረበለት ተናግረዋል።
የጣሊያን ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቴፋኖ ዴ አሌሳንድሪ በበኩላቸው ስምምነቱ የአገራቱን የሁለትዮሽ ትብብር የሚመለከቱ መረጃዎችን እንዲሁም፣ ዓለም አቀፍ ዜናዎችን እንዲለዋወጡ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ስምምነቱ ከተቋማቱ ባለፈ ሁለቱን ሀገራት የበለጠ እንዲቀራረቡ ለማድረግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተዋል።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማት የሆኑት ደሳለኝ ስዩም ስምምነቱ ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ያላቸውን የረጅም ዓመት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ጣልያን በባህል፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካ ዘርፎች እንዲሁም በሚዲያው ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት ቀጣይነት እንዲኖረው ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አመልክተዋል።
አጄንዚያ ናዚናሌ ስታምፓ አሶሲያታ /ANSA/ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1945 የተመሰረተ ሲሆን ዜናዎችን ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች መረጃዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ተቋም ነው።
ኢዜአ በ1934 ዓ.ም የተቋቋመ በስምንት የአገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ የሚያደርግ አንጋፋ የዜና አገልግሎት ተቋም መሆኑ ይታወቃል።
በበይነ መረብ በተካሄደ የመግባቢያ ስምምነት ዋና ስራ አስፈጻሚዎቹን ጨምሮ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴን ጨምሮ ሌሎችም ተሳትፈዋል።