ቀጥታ፡

የባህር በር ጥያቄ ዘመናትን የተሻገረ የመላው ህዝብ ጥያቄ በመሆኑ አስፈላጊነቱን ለማስረዳት በቁርጠኝነት እንሰራለን -የዩኒቨርሲቲ ምሁራን

ሶዶ፣ ጥር 10/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ዘመናትን የተሻገረ የመላው ህዝብ ጥያቄ በመሆኑ አስፈላጊነቱን ለማስረዳት በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በዩኒቨርሲቲው "ያልተቋረጠው የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ታሪካዊ፣ ጂኦፖለቲካዊና ከባቢያዊ አተያይ" በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው። 

በውይይቱ  ላይ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጉቼ ጉሌ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ወሳኝነትን ከማረጋገጥ አኳያ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤና ምክረ ሃሳቦችን የመፍጠር ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል። 

በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የታሪክና የህግ ምሁራንን ጨምሮ ከሌሎች ምሁራን ጋር በባህር በር ጥያቄ ዙሪያ ታሪካዊ ዳራና አካሄዱን በማሳወቅ ረገድ ሳይንሳዊ ምክረ ሃሳቦችን የማፍለቅ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ስኬታማነት የመንግስት ሀላፊነት ብቻ አለመሆኑን ጠቁመው በሀገር ውስጥ ሆነ በውጪ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አጋርነት የሚሻ ነው ብለዋል። 

በመሆኑም ዩኒቨርስቲው ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ አመልክተዋል። 

''የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የቆየ የህልውና ጥያቄ ነው'' ያሉት ዶክተር ጉቼ ጉዳዩን በተመለከተ ከሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተከታታይ ስራዎች እንደሚሰሩ አስረድተዋል። 

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አበሻ ሽርኮ በበኩላቸው በታሪክ ኢትዮጵያን ከባህር በር ነጥሎ ማየት አይቻልም ይላሉ። 

ምክንያቶች ቢኖሩም በአጋጣሚ የባህር በር የማጣት ዕጣ የደረሳት ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት ትውልዱ ሲጠይቀው የኖረበት ጥያቄ መሆኑን አንሰተው ይህ እንዲሳካ የሁሉም ጥረት ይጠይቃል ነው ያሉት። 

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት ጉዳዩን በትኩረት እንዲከታተሉ ከማስቻል አኳያ የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ  እንደሚገባ ተናግረዋል። 

በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ማርቆስ፣ ''የሀገራችን የባህር በር ጥያቄ ዘመናትን የተሻገረ የመላው ህዝብ ጥያቄ ነው'' ብለዋል።

የባህር በር ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቄሜታ አንጻር የተፈጠሩ ስህተቶችን ለማረምና ህጎች በሚፈቅደው መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆን መንግስት የጀመራቸው አካሄዶች ተገቢነት ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ከሶማሌላንድ ጋር ወደብን በጋራ የማልማትና የመጠቀም የመግባቢያ ስምምነት መፈረም እስከመቻል መድረሱ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መሆኑን ተናግረዋል። 

ስምምነቱን አስመልክቶ ካለው እውነታ የራቁና የተሳሳቱ መረጃዎች እየተሰራጩ መሆኑን አውስተው የባህር በር ጉዳይ የሀገራችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ወሳኝ ሂደት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል። 

የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ እንዲረጋገጥ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የዓለምአቀፍ ህጎችና ተያያዥ ተሞክሮዎችን መቃኘት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በፓናል ውይይቱ ላይ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጉቼ ጉሌ፣ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን፣ የዞንና ወረዳ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች እየተሳተፉ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም