18ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ሕብረ ብሄራዊ አንድነት የተረጋገጠበት ነው -አቶ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
18ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ሕብረ ብሄራዊ አንድነት የተረጋገጠበት ነው -አቶ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2016 (ኢዜአ)፦ በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተከበረው 18ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ሕብረ ብሄራዊ አንድነት የተረጋገጠበት ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት 18ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ሕዝቦች በዓል በስኬት መጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ሰጥቷል።
በዓሉ በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለ5 ተከታታይ ቀናት የተከበረ ሲሆን በሕዝቦች መካከል የባህልና እሴቶች ልውውጥ ተደርጎበታል።
ከዚህ ባለፈም በሕገ-መንግስት አስተምህሮ፣ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችና የመግባባት ዲሞክራሲ ጽንሰ ሀሳቦች ላይ ትኩረት ያደረጉ የፓናል ውይይቶች መካሄዳቸው ይታወቃል።
ለበዓሉ አከባበር ስኬታማነት አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል የሱማሌ ክልል፣ የክልሎችና ከተማ መስተዳደር ምክር ቤቶች፣ የጸጥታ መዋቅሮችና መገናኛ ብዙኃን እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤18ኛው የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ሕዝቦች በዓል ዓላማውን በማሳካት ውጤታማ ሆኖ ተጠናቋል።
ለዚህም የሱማሌ ክልል አመራሮች፣ የፌዴራልና የሱማሌ ክልል ጸጥታ መዋቅር ቅንጅት ከመገናኛ ብዙኋን ተቋማት ትጋት ጋር ተዳምሮ በዓሉ ውጤታማ በሆኑ መልኩ እንዲከበር አስችሏል ነው ያሉት።
በዓሉ በሕዝቦች መካከል የበለጠ መቀራረብ መፍጠር ያስቻለ መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባኤው ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ወንድማማችነትን ማረጋገጥ ያስቻለ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።
እንደ አቶ አገኘሁ ገለጻ መገናኛ ብዙኃን የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ሁነቶችን ከመዘገብ ባለፈ በሱማሌ ክልል ያሉ የልማት እድሎችና አማራጮችን በመዘገብ ረገድ ምሳሌ የሚሆን ሥራ አከናውነዋል።
ባለኃብቶችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም በገንዘብና በሀሳብ ያበረከቱት አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸው ይሄው ልምድ ሊሰፋ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በበኩላቸው፤ በዓሉ በክልሉ መከበሩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በፍጥነት እንዲከናወኑ ማስቻሉን አንስተዋል።
በዓሉ የሕዝቦችን ትስስር ከማሳለጥ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑንም አመልክተዋል።
በቀጣይ በዓሉን የሚያዘጋጁ ክልሎች በመሰረተ ልማት አቅርቦትና ግንባታ መስክ ሰፊ ሥራዎችን ቢያከናውኑ የተሻለ ውጤት እንደሚያገኙ የሱማሌ ክልል ማሳያ ነው ብለዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ብዝሃነትና የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ትግሉ መለሰ በበኩላቸው በዓሉ ረዘም ላለ ጊዜ መከበሩ በሕዝቦች መካከል ያለው መቀራረብ ይበልጥ እንዲጎላ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በብሄራዊ መግባባት ላይ የተመሰረቱና አንድነትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚሰራበት ተናግረዋል።
ቀጣዩ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ እንደሚካሄድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።