ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው የለውጥ ሂደት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ ታሪክ ሊሰሩ ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው የለውጥ ሂደት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ ታሪክ ሊሰሩ ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2016 (ኢዜአ)፦ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ማንም ወደ ኋላ በማይመልሰው የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ ታሪክ ሊሰሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት ለገቡ ኢትዮጵያውያን ይፋዊ የአቀባበል መርሐ ግብር በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከአሜሪካ፣ አውሮፓና ሌሎችም የዓለም ክፍሎች የመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት የሚያደርጉት ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራት በቅንጅት እየተሰሩ ነው።
ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መምጣታቸው ባህላቸውን፣ ታሪካቸውንና ማንነታቸውን በመረዳት ስለሀገራቸው ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንዲይዙ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
ወደ ሀገራቸው የመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለችበትን ሁኔታ እንዲመለከቱ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
"ስለ ሀገራችሁ ይዛችሁ የምትሄዱትና ለዓለም የምትናገሩት ብዙ ነገር አለ" ያሉት ከንቲባዋ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቆይታቸው ድንቅ የለውጥ ስራዎች እንደሚመለከቱ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ኋላ መመለስ የማትችልበት ለውጥ ውስጥ መግባቷን በመናገር ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በዚህ ረገድ የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ ታሪክ እንደሚጽፉ ያላቸውን አምነት ገልጸዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ አስፈላጊና የማይተካ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንም ሀገራቸውን ከማወቅ ጀምሮ የተሻለ ነገን በመገንባት ሂደት ተሳታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዝዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ለኢዜአ እንደገለጸው ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው በበጎ ተግባር ላይ እንዲሳተፉ የአዲስ አበባ ዲያስፖራ ማህበር የተጠናከረ ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛል።
ማህበሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ታሪክ፣ ባህልና ማንነታቸውን እንዲያውቁ በክልል ከሚገኙ የዲያስፖራ ቢሮች ጋር በመተባበር እየሰራ ነው ብሏል።
ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲጎበኙ የቀረበው ጥሪ ሀገራቸውን በሚገባ እንዲያውቁ በር የሚከፍት መሆኑንም ነው የተናገረው።
በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያንም የሀገራቸውን ባህልና ታሪክ በመረዳት ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኘውና ከጀርመን የመጣው የ11 ዓመቱ ታዳጊ ሀቢብ ሙደሲር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።
በቆይታውም በሀዋሳ፣ ቢሾፍቱ፣ እንዲሁም በወዳጅነት ፓርክ ድንቅ የሆኑ ነገሮችን መጎብኘቱን ገልጿል።
ከሳዑዲ አረቢያ የመጣው አብዱልአፋር አማር አህመድ ጥሪው ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲያውቁ በር የከፈተ ነው ብሏል።
በቆይታው ኢትዮጵያ ድንቅና ውብ ሀገር መሆኗን መመልከቱን ተናግሯል።
ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቆይታቸው ሀገራቸውን የሚጎበኙበትና ታሪክና ባህላቸውን የሚያውቁበት ልዩ ልዩ መርሐ ግብር መዘጋጀቱን በመድረኩ ተገልጿል።
በመዲናዋ በድምቀት በሚከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል እንዲሁም የአድዋ ድል በዓል ላይ እንዲገኙና እንዲሳተፉም ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።