በሲዳማ ክልል የከተራና ጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል- የክልሉ ፖሊስ

ሀዋሳ፤ ጥር 9/2016 (ኢዜአ)  በሲዳማ ክልል የከተራና ጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የጸጥታ ሃይሉ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራና የተቀናጀ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን  የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ። 

ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በቅንጅት የሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በበኩላቸው የበዓሉ  በሰላም መከበር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የሚጠበቅብንን እንወጣለን ብለዋል ። 

የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የከተራና ጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ሃይሉ ከህብረተሰቡና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል። 

ኮሚሽኑ ከፌደራል፣ ከክልልና ከተማ ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ለተከታታይ ቀናት በአደባባይ የሚከበረው በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል። 

ኮሚሽኑ ከሀዋሳና ከክልሉ ነዋሪዎች፣ የእምነት ተቋማትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በበዓሉ አከባበርና በሰላም ዙሪያ መወያየቱንም ገልጸዋል። 

ለበዓሉ ከክልሉና ከክልሉ ውጭ የሚመጡ እንግዶችን ህዝቡ በጨዋነት እንዲያስተናግድ ጠይቀው ሆቴሎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ያለምንም ጭማሪ እንዲያስተናግዱ ምክክር ተደርጓል ብለዋል። 

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በሀዋሳ ከተማና በተለያዩ ወረዳዎች የፖሊስ መረጃ ማዕከላትን በአዲስ መልክ ማደራጀቱን የገለጹት ኮሚሽነሩ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተቋቋሙ ጊዜያዊ ችሎቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል። 

በኮሚሽኑ የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ተወካይ ኮማንደር ከበደ ኬኔራ በበኩላቸው የጥምቀት በዓል ከፍተኛ ሕዝብ በአደባባይ የሚያከብረው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለተሸርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች እንደሚኖሩ ተናግረዋል ። 


በሃዋሳና በክልሉ አራቱም ዞኖች በዓሉ በድምቀት በሚከበርባቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳያጋጥም የሚመለከታቸውን አካላት ያሳተፈ ውይይትና ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።  

ወጣት ሃብታሙ ሳሙኤል፤ ''ሱሙዳ አደባባይ'' ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በማህበር ተደራጅተው ፎቶ ከሚያነሱ ወጣቶች መካከል አንዱ ሲሆን ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት በአሉ በሰላም እንዲከበር የመስራት ልምድ እንዳላቸው ተናግሯል። 


 

ከክልልና ከከተማ የፀጥታ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት በበዓል አከባበር ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ወንጀሎችን በጋራ የመከላከል ስራ በመስራት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጿል። 

የሱሙዳና አካባቢው ሰላም ፎቶ አንሺ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት አዲሱ አለማየሁ በበኩሉ ስራቸው ከበዓላትና ከሰላም ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ የበዓሉ በሰላም መከበር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሷል።


በመሆኑም ከፎቶ ከማንሳቱ ጎን ለጎን ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር በዓሉ በሰላም እንዲከበር የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግሯል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም