በክልሉ የፖሊስን አቅም የማጠናከርና የማጎልበት ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የፖሊስን አቅም የማጠናከርና የማጎልበት ተግባር እየተከናወነ ነው
ቦንጋ ፤ ጥር 9/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፖሊስ ሃይል አቅምን የማጎልበት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን መካከለኛና ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖችን ዛሬ አስመርቋል ።
በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በክልሉ የፖሊስ ሃይልን የማጎልበትና የማብቃት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ።
ከዚህ ቀደም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ይስተዋሉ የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ተፈተው ሰላም መስፈኑን ጠቁመው ለዚህም የፖሊስ ሀይል ማህበረሰቡን በማሳተፍ ተግባሩን ከመወጣት ባለፈ ተኪ የሌለው መስዋዕትነት መክፈሉን ገልጸዋል።
ሰላማዊና ልማት ላይ ያተኮረ ክልልን ለመፍጠር የተጀመሩ ተግባራትን ከግብ ለማድረስ የፖሊስ ሃይልን ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ይህንንም የክልሉ መንግስት አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ለዚህም ጊዜውን የዋጀ ስልጠና፣ የማዕረግ ማሳደግና አደረጃጀትን የማጠናከር ስራ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አንድነት በዛሬው ዕለትም ለመጀመሪያ ጊዜ ክልሉ ያሰለጠናቸውን መኮንኖች ማስመረቅ መቻሉን ተናግረዋል።
የክልሉን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ከማድረግ አንፃር ዛሬም ቀሪ ስራዎች አሉ ያሉት አቶ አንድነት፣ ክልሉ ያለውን ሀብት ወደ ልማት በመቀየር ለብልፅግና መጠቀም እንዲቻል ከፖሊስ ብዙ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
ዛሬ የማዕረግ ሽግግርና የአቅም ግንባታ ስልጠና የወሰዱ የፖሊስ አባላት ተጨማሪ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው በመገንዘብ የፖሊስ ስብዕናን በመላበስ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብስቤ ሻወኖ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በክልሉ የፖሊስ ኃይል አቅምን የማጠናከርና የማብቃት ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ።
በክልሉ ሰላምን ለማጽናት የፖሊስ ሃይሉን አቅም በዕውቀትና በሌሎች አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች የማሳደግና የማብቃት ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።
ይህም በክልሉ የሚገኙ የፖሊስ ሃይሎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አንዲወጡ በማድረግ ሰላም የሰፈነበትና ልማት ላይ ያተኮረ ክልል ለመፍጠር ታስቦ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ፖሊስ ኮሚሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት በየዞኖቹ ያሉ ችግሮችን በመለየት ህዝብን ባሳተፈ የወንጀል መከላከል ስራና ስምሪት በመስጠት በሁሉም አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን ማድረጉን ጠቅሰው ለዚህ ውጤት የፖሊስ ሃይሉ ሚና የላቀ መሆኑን አንስተዋል ።
በመሆኑም የዛሬ ምሩቃንን ጨምሮ በክልሉ ያሉ የፖሊስ ሃይሎች እያበረከቱት ያለው የሰላም ማስጠበቅ ስራ እንዲጠናከር ኮሚሽኑ ከሙያ ስነ ምግባር ጨምሮ እስከ ሙያዊ ዕውቀትና ግብአት የማደራጀትና የማብቃቱን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የስልጠናው አስተባባሪ ኮማንደር ፈቀደ ከበደ "የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ትልቅ ሀላፊነት የተሰጠው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ይህን ውጤታማ ለማድረግ የፖሊስ አባላቱን አቅም በማሳደግ ላይ ይገኛል" ብለዋል።
ሰልጣኞች በስልጠና ቆይታቸው ከዘመኑ ዕድገት ጋር ተያይዞ እየረቀቀ የመጣውን የወንጀል ድርጊት መከላከልና ሰላምን ለማጽናት የሚያስችል ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም ተመራቂ የፖሊስ አባላት በስልጠና ቆይታቸው ባገኙት ዕውቀት በመታገዝ ፖሊሳዊ ስነ-ምግባርን በጠበቀ መልኩ ግዳጃቸውን በብቃት እንዲወጡም አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገብረማሪያም ፖሊስ ሁሉንም በእኩልነትና በታማኝነት በማገልገል የተሰጠውን ለፍትህ መስፈን የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ዛሬ በተከናወነ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ለተመራቂ የፖሊስ መኮንኖች የማዕረግ ማልበስ ስነስርዓት የተከናወነ ሲሆን፣ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡና ለስልጠናው መሳካት ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱት የምስክር ወረቀትና ሽልማት ተበርክቷል።