በኢትዮጵያ ህጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ አገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል - የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ህጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ አገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል - የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ህጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ አገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
ያለ ሕጋዊ ሰነድ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ዜጎች ከጥር 1 እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ተቋሙ በመቅረብ ሕጋዊ ሰነድ እንዲይዙ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ማሳሰቡ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ህጋዊ ፈቃድ ሳይዙ የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገራት ዜጎችን በተመለከተ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በህገወጥ መንገድ የሚወጡና የሚገቡ ዜጎችን መቆጣጠር የሚያስችል የድንበር ፖሊስ የሚባል አሀድ እንዳለውም ገልጸዋል።
በዚህም በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ተታለውና ገንዘብ ከፍለው ከሀገራቸው የሚወጡትን በመያዝ ለሚመለከተው አካል በማስረከብ ስልጠና ወስደው ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ በጎረቤት ሀገራት ካለው የጸጥታ ችግር አንጻር በርካታ የውጭ አገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡም ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በመላ ሀገሪቱ ስምሪት ውስዶ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተልዕኮ እንደተሰጠው ጠቅሰው፤ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት በሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ ራሱን አዳብሯል ብለዋል።
የፌዴራል ፖሊስ የድንበር ፖሊስና ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ከክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር በድንበር አካባቢ ያሉ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን እየተቆጣጠሩ እንደሚገኙም አንስተዋል።
በመሆኑም ማንኛውም የውጭ ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ህጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የመያዝ ግዴታ አለበት ነው ያሉት፡፡
ነገር ግን በተለያየ መንገድ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ቀርበው ህጋዊ ሰነድ መያዝ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ይህ ካልሆነ ግን ህግን መሰረት ባደረገ አግባብ በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል፤ የቁጥጥር ሥራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡