በሀዋሳ ሐይቅ የሚከበረውን የከተራ በዓል ካለፈው አመት በተሻለና በደመቀ መልኩ ለማክበር ከቤተክርስቲያንና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ ሐይቅ የሚከበረውን የከተራ በዓል ካለፈው አመት በተሻለና በደመቀ መልኩ ለማክበር ከቤተክርስቲያንና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው
ሀዋሳ፤ ጥር 09/2016 (ኢዜአ) በሀዋሳ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ሐይቅን አቋርጦ በመጓዝ የሚከበረውን የከተራ በዓል ትዕይንት በተሻለና በደመቀ መልኩ ለማክበር ከቤተክርስቲያኑና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ገለፀ ፡፡
ሀዋሳ የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ ናት።
ከሀዋሳ ሀይቅ ማዶ ከምትገኘው የሎቄ ደብረ መድኃኒት መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ተነስቶ ሐይቁን አቋርጦ በማለፍ የሚከበረው የከተራ በዓል ለከተማዋ ተጨማሪ ሳቢ የጥምቀት ገፅታን የቸራት ነው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መቅደስ ሁሪሶ በሀዋሳ ዘንድሮ ሐይቅን አቋርጦ በመጓዝ የሚበረውን የከተራ በዓል ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ታቦታቱ የሀዋሳ ሀይቅን በማቋረጥ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክዋኔዎችና የጀልባ ትርዒቶች ታጅበው የሚመጡበት ስርዓት ለአይን ማራኪና እጅግ ሳቢ መሆኑን አንስተው ይህም ሁነት የቱሪዝም ሀብትን ያሳድጋል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከቤተክርስቲያኒቱ፣ ከጀልባ ማህበራትና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር በዓሉ ከአምናው በተሻለ ድምቀት እንዲከበር እየሰራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት ።
የሀዋሳ ከተማ ባላት ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህብነት እንደምትታወቅና ህዝባዊና ሐይማኖታዊ በዓላትም በድምቀት የሚከበሩባት ከተማ እንደሆነችም አስረድተዋል።
"ለክብረበዓሉ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጡ ጎብኚዎች በከተማዋ ጥሩ ጊዜን እንዲያሳልፉ ዝግጅት አድርገናል" ብለዋል።
በሀዋሳ ለከተራ በዓል ታቦታቱን ይዞ ሐይቅን የማቋረጥ ሥርዓት አምና ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው በከተማዋ ከሀዋሳ ሐይቅ ማዶ ሎቄ አካባቢ ከሚገኘው የሎቄ ደብረ መድኃኒት መስቀለ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን እንደሆነ የጠቀሱት ደግሞ የደብሩ አስተዳዳሪ መልዓከ ፀሐይ ቀሲስ ለቤዛ አለሙ ናቸው።
በዓሉ ከአምናው በተሻለ ድምቀትና ሥርዓት በጠበቀ መልኩ እንዲከበር በየዘርፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመናበብ ሰፊ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማህበረ ምዕመናን፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እንዲሁም ዝግጅቱን ከሚያስተባብሩ የኮሚቴ አባላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የገለፁት።
የደብረ መድኃኒት መስቀለ ክርስቶስ ቤተክርሲቲያን ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበርና የበዓሉ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አንተነህ ተሾመ ክብረ-በዓሉን ከአምናው በተሻለ የደመቀ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በአሁን ወቅት ለበዓሉ ዝግጁ የሆኑ ጀልባዎች ቁጥር ከዓምናው ከእጥፍ በላይ ማደጉን ጠቅሰዋል።