"አድዋን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ " በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የንቅናቄ ፎረም ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
"አድዋን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ " በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የንቅናቄ ፎረም ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2016(ኢዜአ)፦ "አድዋን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ " በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የንቅናቄ ፎረም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዛሬ መጀመሩን ሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሰላም ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሀገር አቀፍ የሰላምና የሀገር ግንባታ ንቅናቄ መርሀ ግብር በዛሬው እለት መጀመሩን ይፋ አድርጓል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች "አድዋን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ " በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ፎረም ዋና ዓላማ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ላይ ያስመዘገቡት ድል ዜጎች በአንድነትና በአብሮነት ለጋራ ዓላማ በጋራ ከቆሙ መፍታት የማይቻል ችግር አለመኖሩን የሚያስተምር ነው ብለዋል።
ከዚህ አኩሪ ድል ኢትዮጰያዊያን ትልቅ ትምህርት በመውሰድ የተሻለችና ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር ለመገንባት በአንድነት ልንቆም ይገባል ብለዋል።
ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ከሚገባቸው ባለድርሻ አካላቶች ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተጠቃሽ መሆናቸውን አክለዋል።
በዚህም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "አድዋን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ " በሚል መሪ ቃል እስከ የካቲት 21 ቀን የሚቆየው የንቅናቄ ፎረም በይፋ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ሀገራዊ ማንነትንና እሴቶችን የተመለከቱና በኢትዮጵያዊ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ምክክሮች እንደሚካሄዱ አብራርተዋል።
ቀደምት አያቶቻችንን ያለምንም ልዩነት በአድዋ ያስመዘገቡትን አኩሪ ታሪክ መነሻ በማድረግ የአሁኑ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጠንካራ አገር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ንቅናቄው ሀገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እና በተለያዩ አካላቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰከነ መንፈስ ለመፍታት የሚቻልበትን አቅጣጫ ያመላክታል ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው እንደ ሀገር በተለያዪ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መወያየትን የሚመርጥ ማህበረሰብ ለመፍጠር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።
አባቶቻችን በአንድነት በመቆም በአድዋ ጦርነት ያስመዘገቡት ድል ኢትዮጵያን በነፃነት በማቆም ለአሁኑ ትውልድ ለማስረከብ አስችሏቸዋል ብለዋል።
ከአድዋ ድል ትምህርት በመውሰድ በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቱን እየፈተኗት ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት በጋራ በመቆምና በመነጋገር መፍትሄ ማበጀት ይኖርብናል ነው ያሉት።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረገው የንቅናቄ ፎረም ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 21 ቀን 2016 የሚቆይ ሲሆን በመድረኩ ከትምህርት ማህበረሰቡ በተጨማሪ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል።