ቀጥታ፡

አየር መንገዱ በመቀሌ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ መጠነኛ ጉዳት ያጋጠመውን አውሮፕላን ክስተት በተመለከተ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመቀሌ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ መጠነኛ ጉዳት ያጋጠመውን የመንገደኞች አውሮፕላን በተመለከተ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።

ኢቲ 106/18 የተሰኘው የመንገደኞች አውሮፕላን ከቀኑ 6፡30 ከአዲስ አበባ ተነስቶ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በማረፍ ላይ ሳለ መጠነኛ ችግር እንዳጋጠመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል።

በክስተቱ ተጓዦችም ሆነ የበረራ አስተናጋጆች ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ነው አየር መንገዱ በመግለጫው ያስታወቀው።

ለተፈጠረው ክስተት ውድ ደንበኞቻችንን ይቅርታ እንጠይቃለን ያለው አየር መንገዱ ያጋጠመውን ችግር ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅም ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ በመግለጫው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም