ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል የትህትናና የፍቅር ተምሳሌት በመሆኑ ምዕመናን በዓሉን በፍጹም መዋደድ በአብሮነት ሊያከብሩት ይገባል- የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2016 (ኢዜአ)፦ የጥምቀት በዓል የትህትናና የፍቅር ተምሳሌት በመሆኑ ምዕመናን በዓሉን በፍጹም መዋደድ በአብሮነት ሊያከብሩት እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለፁ ፡፡

ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ በባህረ ዮርዳኖስ በዮሃንስ እጅ መጠመቁን በማሰብ የሚከበር ታላቅ በዓል ነው፡፡

የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጡሩ በመጥምቁ ዮሃንስ እጅ በመጠመቅ ትህትናን ያስተማረበት መሆኑን የሃይማኖት አባቶቹ ተናግረዋል።

በዓሉን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አባቶች እንዳሉት በዓሉ "የእግዚአብሄር ክብርና ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር" የተገለጸበት ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ መላዕከ ሰላም አባ ቃለፅድቅ (ዶክተር) እንዳሉት ጥምቀት ቃሉ ተጠምቀ፤ ተጠመቀ፣ ተዘፈቀ፣ ተነከረ የሚል ትርጉምን የሚሰጥ ነው።

ጥምቀተ ክርስቶስ በአደባባይ በድምቀት የሚከበር ብሄራዊና አለም አቀፋዊ ይዘት የተላበሰ በዓል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ጥምቀት ምስጢረ ስላሴ የተገለጸበት፣ የሰው ልጅ የዕዳ ደብዳቤ የተደመሰሰበትና ወደ ክርስቶስ መንግስት መግቢያ በር መሆኑንም አስረድተዋል። 

 የጥምቀት አስተምህሮ አሁን ላለንበት ጊዜ ምሳሌ መሆኑን አንስተው ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፍጡሩ ዮሃንስ ወርዶ በመጠቀም ትህትናን ያስተማረበት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የካፑቺን ማኅበር የልማትና ሐዋርያዊ ስራዎች አስተባባሪ አባ ኃይለገብርኤል መለቁ (ዶክተር) በበኩላቸው የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በመምጣት በዮሃንስ እጅ በመጠመቅ ትህትናን ያሳየበት ነው ብለዋል።


የጥምቀት በዓል ክርስትያኖች የክርስትና ህይወታቸውን የሚያሰላስሉበትና የሚያጤኑበትን እድል የሚሰጥ መሆኑንም ገልፀዋል። 

ምዕመናን በዓሉን ሲያከብሩ  ልዩነትን በመተው በአንድነት ሊሆን እንደሚገባ ነው የሃይማኖት አባቶቹ የመከሩት።

የሃይማኖት አባቶቹ ጥምቀት "ሰላምን በመፍጠርና ለሰላም አርአያ" በመሆን ስለሚከበር ምዕመናን በዓሉን በሰላምና በአንድነት ሊያከብሩት ይገባል ነው ያሉት።

በዓሉን  ስለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በማሰብና በመፀለይ ማክበር እንደሚገባም ነው የገለፁት።

የሃይማኖት አባቶቹ በዓሉ የሰላምና የጤና እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውንም  አስተላልፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም