ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየሰሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2016(ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናሲዮ ካሲስ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ የሁለቱን ሃገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚያሰችላቸው ጉዳዮችና በባለብዙ ወገን መድረኮች በሚኖራቸው ትብብር ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል።

አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ መስክ የሁለቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ምቹ ጊዜ እንደሆነ አንስተዋል።


 

ኢትዮጵያ እየተገበረች ስላለው ሃገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ እንደ ቴሌኮም ያሉ ክፍለ ኢኮኖሚዎችን ክፍት ያደረገች መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ የፋይናንስ ዘርፉም በተመሳሳይ ክፍት እንደሚሆን ገልፀዋል።

የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች በተጠቀሱት እና ሌሎች ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት በሆኑ መስኮች ተሳታፊ በመሆን እያደገ ባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተሳትፎ እንዲኖራቸውም ጠይቀዋል።

አቶ ደመቀ ስዊዘርላንድ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባልነቷ ለምታንፀባርቀው ሚዛናዊ አቋም ምስጋና አቅርበው ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የስዊዘርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናስዮ ካሲስ በበኩላቸው በሁለትዮሽ እና አለምአቀፍ ጉዳዮች የሃገራቱን ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎት ገልፀዋል።

በቀጣይ መጋቢት ወር በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዳቸውን ሚኒስትሩ ጨምረው የገለፁ ሲሆን ጉብኝቱ የሃገራቱን ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ለማስፋት እንደሚያስችል መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም