ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናው አገራት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት ልዩ በረከት ነው- ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2016(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናው አገራት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት ልዩ በረከት መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሁን ላይ ከዓለም ቀዳሚ የትኩረት አጀንዳዎች መካከል ኢነርጂ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የህዳሴ ግድብ መገንባቱ ከሀገሪቷ አልፎ ቀጣናዊ ልማትና ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በርካታ ሀገራት የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅና ሌሎች የኃይል ምንጮችን በመጠቀም ቢበለጽጉም፤ እነዚህ የኃይል ምንጮች በካይ በመሆናቸው ከባቢ አየሩና ስርአተ ምህዳሩ ስለመጎዳቱ አንስተዋል።

የበለጸጉትም ይሁን በማደግ ላይ ያሉ አገራት ለዓለም ስርዓት ዘላቂነትና ለአካባቢ ምህዳር መጠበቅ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ቀዳሚ ትኩረት እያደረጉ መጥተዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያም በውሃ፣ ፀሐይ፣ ጂኦተርማል፣ ነፋስ ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል አቅም ያላት ሲሆን በዓለም ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራትም ጠቁመው፤ ለቀጣናውና ለዓለም በምታበረክተው ልክ መጠቀም ይገባታል ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደም የተገነቡ የውሃና የነፋስ ኃይል ማመንጫዎችም የሀገርን እድገት ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚወስድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሀገሪቷም አልፎ ለቀጣናው አገራት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት ልዩ በረከት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቀጣናው የኃይል መሰረተ ልማተ ትስስር ላይ አበክራ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው የውሃ ሀብቷን ስታለማ ጎረቤቶቿን በሚጠቅም ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ለሱዳን፣ ለጅቡቲ እና ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ መሆኗን ጠቅሰው በቀጣይ ለሌሎችም ተደራሽ ለማድረግ ትሰራለች ብለዋል።

በመሆኑም በተለይም ጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያን በጋራ የመልማት እቅድ በመደገፍ አብሮነታቸውን ማሳየት አለባቸው ነው ያሉት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የባህር በር ለማግኘት እየተደረገ ያለው ጥረትም ሀገራዊ ጥቅምን ከቀጣናዊ ትብብር ጋር አስተሳስሮ የመሄድ ጉዳይ መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል ብለዋል። 

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከፍተኛ እምቅ የልማት ጸጋ አለው ያሉት  ሚኒስትሩ ፤ ኢትዮጵያም ይህንን አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት እየተጋች ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

የቀጣናውን ሁለንተናዊ ልማት በማፋጠን ወደ ተሻለ የእድገትና ተጠቃሚነት ምዕራፍ ለማሸጋገር በተለይም የጎረቤት አገራት ቅንጅታዊ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም