ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2016 (ኢዜአ)፦የጥምቀት በዓል ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ሒክማ ኸይረዲን ገለጹ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ነዋሪዎች የከተራና የጥምቀት ክብረ በዓላትን በማስመልከት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ  የታቦታት ማለፊያ እና ማደሪያ ስፍራዎችን አጽድተዋል።

በጽዳት ስራው ላይ የተሳተፉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ሒክማ ኸይረዲን፤ የጥምቀት ክብረ በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ወካይ ቅርስ የተመዘገበ የኢትዮጵያ ሃብት በመሆኑ ሁላችንም ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል።

በአሉ ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባልም ነው ያሉት።


 

በኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤ የጽዳት ዘመቻው የአብሮነት፣ መከባበርና መቻቻል እሴቶችን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ አደም አብደላ፤ መሰል ሀይማኖታዊ በዓላት የአንድነታችን ማስተሳሰሪያ ገመድ ናቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም የከተራና ጥምቀት በአላት ሲከበሩ ሰላምና አብሮነትን በሚያጠናከር መልኩ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት በመወከል የተገኙት ፓስተር ሙላቱ ኤርሚያስ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ሁላችንም ባለቤት ሆነን መስራት አለብን ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም