ቀጥታ፡

የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የፍላጎት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው - አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የፍላጎት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለፁ።

አዲስ አበባ ተቀማጭነታቸውን ላደረጉ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎችና አለም አቀፍ ተቋማት በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችውን የባህር በር ስምምነት በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ከአላማው ውጪ የሆኑ የተሳሳቱ መረጃዎች መሰራጨታቸውን አንስተው የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የፍላጎት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

ከሶስት አስርት አመታት በላይ በጅቡቲ ወደብ በኩል የገቢ ወጪ ንግዷን እያከናወነች መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ካለው አገራዊና አለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ አማራጮችን መፈለግ ግድ ይላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና ፀጥታ የህይወት መስዕዋትነት መክፈሏን ጠቅሰው ከሶማሊያም ሆነ ከሌሎች ጎረቤት አገራት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና ኢኮኖሚ ምላሽ መስጠትን ዓላማ ያደረገ እንጂ ማንንም ለመጉዳት አይደለም ሲሉም አስረድተዋል። 

የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተመለከተም ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለክልሉ አመታዊ በጀት ከመመደብ ጀምሮ በጦርነቱ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል ብለዋል።


 

በዚህም መንገድና ድልድዮችን ጨምሮ ባንክ ቴሌኮምና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች መጀመራቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ ተከስቶ በነበረው ጦርነት ወንጀል የፈፀሙ አካላት ላይ አስፈላጊው ማስረጃ በማጠናከር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በክልሉ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም አለም አቀፍ አጋር አካላት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።

የሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም አምባሳደር ሬድዋን አብራርተዋል

በአማራ ክልል የነበረው የጸጥታ ችግርም በመከላከያና በክልሉ የፀጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋሉን አብራርተዋል።

መንግስት ማንኛውንም ችግር በውይይትና በድርድር እንጂ በአፈ-ሙዝ የመፍታት አላማ የሌለው መሆኑን ገልጸው በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማድረጉን ተናግረዋል።

በአሁን ጊዜም በክልሉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን አብራርተዋል፡፡ 

በኦሮሚያ ክልልም ተመሳሳይ የጸጥታ ስራዎችን ለማከናወን የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

እንዲህ አይነት አደረጃጀቶች ህዝቡን ከማሸበርና የራሳቸውን ጥቅም ከማስጠበቅ ውጪ ዓላማ የሌለው ነው ብለዋል።

የትጥቅ እንቅስቃሴን አማራጭ የሚያደርግ አካልም በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በኩል ለመነጋገርና መዘጋጀት አለበት ነው ያሉት።

 

የመከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ፤  ወታደራዊ አታሼዎችና አለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እያበረከተ ላለው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

ወታደራዊ አታሼዎች የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔት በተመለከተ በየማህበራዊ ሚዲያ የሚነዙ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን ለማጥራት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ከመከላከያ ወታደራዊ አመራሮች እውነተኛ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚችሉም ነው የገለጹት።

የየአገራቱ ወታደራዊ አታሼዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ላይ ያለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ በተደረገው ገለጻ ትክክለኛ መረጃ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

መንግስትና የመከላከያ ሰራዊቱ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላምና ደህንነት  ያሳዩትን ቁርጠኝነትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም