በጎንደር በጥምቀት በዓል ላይ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች የተፋጠነ ፍትህ ለመስጠት ጊዚያዊ ችሎት ተቋቋመ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር በጥምቀት በዓል ላይ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች የተፋጠነ ፍትህ ለመስጠት ጊዚያዊ ችሎት ተቋቋመ
ጎንደር፤ ጥር 9/2016 (ኢዜአ)፡- በጎንደር በጥምቀት በዓል ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች የተፋጠነ ፍትህ ለመስጠት የሚያስችል ጊዚያዊ ችሎት መቋቋሙን የከተማ አስተዳደሩ ፍትህ መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የወንጀል ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አስቻለው አብረሃ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በጥምቀተ ባህሩ አካባቢ የተቋቋመው ጊዜያዊ ችሎቱ ዳኞች አቃቢ ህግና ፖሊስ የተመደበለት ነው።
ችሎቱ በበዓሉ ስፍራ እጅ ከፍንጅ የሚያዙ ወንጀለኞች ምርመራቸውን አጣርቶ አፋጣኝ ፍትህ የሚሰጥ መሆኑ ተመልክቷል።
በተጨማሪ በበዓሉ ስፍራ የተከለከሉ የስለት መሳሪያዎችና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዘው የሚገኙ ግለሰቦችም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት ቅጣት ይተላለፍባቸዋል ሲሉም አስታውቀዋል።
በፍርድ ሂደቱ ችሎቱ በኤግዚቢት የተያዙ ንብረቶችንም ባለቤቶቹ በሚያቀርቡዋቸው የህግ ምስክሮች ንብረታቸውን እንዲረከቡ እንደሚደረግ አስረድተዋል።
የችሎቱ መቋቋም በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶች ንብረት ተሰርቀው በመደበኛው ፍርድ ቤት ክስ መስርተው የሚያደርጉት የክርክር ሂደት ጊዜ እንዳይወስድባቸውና እንዳይጉላሉ ለማገዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ችሎቱ ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ክፍት በመሆን አገልግሎት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።