የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ የታለመለትን ግብ አሳክቷል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ የታለመለትን ግብ አሳክቷል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2016 (ኢዜአ)፦ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ የታለመለትን ግብ ማሳካቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዶክተር መለስ ዓለም፤ የዲፕሎማሲ ሳምንትን ጨምሮ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ የታለመለትን ዓላማ ያሳካ ውጤታማ ዝግጅት ነበር ብለዋል።
አውደ ራዕዩ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ፣ የአሁኑንና የመጭውን ጊዜ ለበርካቶች በማሳየት የተሳካ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአጠቃላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አውደ ርእዩን መጎብኘታቸውንም አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ወቅታዊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴን በተመለከተም በሰጡት ማብራሪያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በዳቮስ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ በገለልተኛ አገሮች ጉባኤ ላይ እየተሳተፋ መሆኑንም እንዲሁ።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያና ሶማሊላንድን በተመለከተ የሰጡት መግለጫ ጠቃሚ እንዳልሆነም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።
በርካታ አገሮች በሶማሊላንድ ወደብ እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደር መለስ፣ ለኢትዮጵያ ጥያቄ ተለይቶ ነውር ሊሆን አይችልም ሲሉ ገልጸዋል።