የመግባቢያ ስምምነቱ የእርስ በርስ ትስስር ለማጠናከርና በጋራ ለመልማት ይረዳል - ኢዜአ አማርኛ
የመግባቢያ ስምምነቱ የእርስ በርስ ትስስር ለማጠናከርና በጋራ ለመልማት ይረዳል
ጅግጅጋ ፤ ጥር 9/2016(ኢዜአ)፦ የመግባቢያ ስምምነቱ የእርስ በርስ ትስስር ለማጠናከርና በጋራ ልማት የጋራ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚረዳ በመሆኑ እንደሚደግፉት በሶማሌ ክልል የቶግ ወጫሌ ከተማ የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ ።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የሶማሌላንድ መንግስት በተለያዩ ዘርፎች በቀጣይ ለሚኖር ግንኙነታቸው ማዕቀፍ የሚሆን ታሪካዊ የሆነ የመግባቢያ ሰነድ በቅርቡ በአዲስ አበባ መፈራረማቸው ይታወሳል።
የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ የባህር በር አማራጮችን የሚያሰፋ፣ የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣ የቀጣናው ዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።
ይህን የሰጥቶ መቀበል መርህና የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገውን ስምምነት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና በአካባቢው ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፋቸውን እየሰጡ ነው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ጠረፍ ከተማ ቶግ ወጫሌ ያሉ የአገር ሽማግሌዎች እንዳሉት፤ የመግባቢያ ስምምነቱ የእርስ በርስ ግንኙነትን የሚያጠናክር፣ አብሮ ለመልማት የሚረዳና የሚደገፍ ነው።
ከከተማዋ የአገር ሽማግሌዎች መካከል ኡጋዝ ኢስማኤል ሰሌባን እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት በጋራ የመልማት ሀሳብ በመሆኑ የሚደገፍ ነው።
ባህሩ ቅርባችን ሆኖ ያለ ጥቅም እስከ አሁን ተቀምጧል፤ በዚህ ስምምነት እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ የዓመታት ፍላጎታችንን ያሳካና የሚደገፍ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና ሱማሌላንድ ቶግ ወጫሌ ከተሞች የሚኖሩ ህዝቦች ወንድማማች ናቸው፤ በርካታ የሚያስተሳስራቸው የጋራ እሴቶች አሏቸው፤ በጋራ ሰላማቸውን የመጠበቅ ባህልም አዳብረዋል ብለዋል።
የአገር ሽማግሌው መሐሙድ አሌል በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የመግባቢያ ስምምነቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትስስር ለማሳደግ የላቀ ጥቅም ይሰጣል ብለዋል።
"የወደብ አገልግሎት በስምምነት መጠቀም ኢትዮጵያ የጀመረችው ሳይሆን ዓለም እየተገበረው ያለው አሰራር ነው" ያሉት አቶ መሐሙድ፤ የኢትዮጵያ ለምን እንደ አዲስ ግኝት እየተወራ እንዳለ "ለእኔ ግልጽ አይደለም" ሲሉም ተቃውሞ የሚያቀርቡ አካላትን ኮንነዋል።
የኢትዮጵያና ሱማሌላንድ መሪዎች የተስማሙትን በሙሉ እንደግፋለን ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ አገር ሽማግሌ ሀሰን አደን ዓቅል ናቸው።
የመግባቢያ ስምምነቱ ለሁለቱ ህዝቦች አዲስ የተስፋ ብርሃን የሚሰጥ ነው ያሉት የአገር ሽማግሌው፤ በራሳችን የምናስተዳድረው ወደብ ይኖረናል፤ በነፃነት መጠቀም የሚያስችለን በመሆኑም መቶ በመቶ እንደግፋለን ብለዋል።
የአገር ሽማግሌ አብዲ አደን ፋራህ እንደገለጹት፤ የመግባቢያ ስምምነቱ በትክክለኛ ወቅት ላይ የተፈረመና የህዝቦችን ትስስር ከማጠናከሩም በላይ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።
የቶግ ውጫሌ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙህየዲን አብዲ በበኩላቸው፤ የስምምነት ሰነዱ በህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነትና መተማመንን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በተለያየ መልኩ ጠቃሚነቱ የጎላ ነው ብለዋል።