ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ ቤተሰቡ ይጠበቃል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ይካሄዳል።

በ18 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በፕሪሚየር ሊግ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት ገጥሞታል።

የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን በሁለቱ ተሸንፎ በሁለቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ፈረሰኞቹ ተጋጣሚያቸውን በግብ ክፍያ በልጠው በተመሳሳይ ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ በ2015 ዓ.ም የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል።

ሌላኛው የ11ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን መርሐ ግብር ሀምበሪቾ ዱራሜና ሻሸመኔ ከተማን ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ያገናኛል።

ሀምበሪቾ ዱራሜ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቶ በ 3 ነጥብ በሊጉ የመጨረሻው ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሻሸመኔ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሽንፈት ሲገጥመው በሶስቱ አቻ በመውጣት በ4 ነጥብ 15ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ላይ ተቀምጧል።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉት ሁለቱ ክለቦች እስከ አሁን በሊጉ ምንም ጨዋታ አላሸነፉም።

በተያያዘም በ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ መድንን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 26 ከፍ በማድረግ የሊጉ መሪነቱን አጠናክሯል።

በሌላኛው ጨዋታ መቻል ድሬዳዋ ከተማን 3 ለ 1 በመርታት በ26 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም