የቶግ ውጫሌ ከተማን እድገት ለማፋጠን የሚያግዙ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በመከናወን ላይ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የቶግ ውጫሌ ከተማን እድገት ለማፋጠን የሚያግዙ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በመከናወን ላይ ይገኛሉ

ጅግጅጋ ፤ጥር 09/2016 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል የቶግ ውጫሌ ከተማን እድገት ለማፋጠንና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የሚያግዙ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሙህየዲን አብዲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጠረፍ ከተማ በሆነችው ቶግ ውጫሌ በአሁኑ ወቅት በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደባት ነው።
የከተማዋን ልማት በማስፋፋት የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የአስር ዓመት የማስተር ፕላን ዝግጅት መጀመሩን ከንቲባው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ሶማሌላንድን የምታዋስነው የቶግ ውጫሌ ከተማን እድገቷን በማፋጠን የንግድ ማዕከልነቷን ለማሻሻል በከተማ አስተዳደሩ፣ በፌዴራል መንግስትና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በመገንባት ላይ ካሉት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በአነስተኛ ወጪ የሚገነቡ 20 መኖሪያ ቤቶችና ጤና ጣቢያ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በቶግ ውጫሌ ከተማ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች የነዋሪውን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል።
የነዋሪዎቿን የውሃ ችግር ለመፍታት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመደበው ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ባለፈው ዓመት የተጀመረው የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ 47 በመቶ መድረሱን የገለጹት ደግሞ በሶማሌ ክልል ውሃ ስራዎች ኢንተርፕራይዝ የቶግ ውጫሌ የውሃ ፕሮጀክት ተወካይ አቶ ሀሰን መሀመድ ናቸው።
የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በሚቀጥሉት ስምንት ወራት እንደሚጠናቀቅ አመልክተው፤ በፕሮጀክቱ እስካሁን የስድስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቆፋሮ ተጠናቆ የማገናኘት ስራው ተሰርተዋል ብለዋል።
ከከተማው አስር ኪሎ ሜትር ርቀት አከባቢ 1 ሺህ 500 ሜትር ኪዮብ ውሃ መያዝ የሚያስችል የውሃ ማጠራቀሚያ ግንባታም በመካሄድ ላይ ነው ሲሉም ገልጸዋል።