ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው የባህር በር ስምምነት የኢንዱስትሪ ልማትን ለማነቃቃት የላቀ ሚና ይኖረዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው የባህር በር ስምምነት የኢንዱስትሪ ልማትን ለማነቃቃት የላቀ ሚና የሚኖረው መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ልማት ኮርፖሬሽን አመራርና ሠራተኞች በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የባህር በር ስምምነት ፋይዳ በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ፤ የተደረገው ስምምነት ዲፕሎማሲውን የሚመጥን፣ በጥበብ የተመራ እና የላቀ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።

የባህር በር ስምምነቱ ከኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባለፈ ለአህጉራዊ የጋራ ልማትና እድገት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ስምምነቱ ከኢትየጵያ ታሪካዊ ሁነቶች መካከል የሚቆጠር እና የኢትዮጵያ ሕዳሴ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ሀገር ካለው ትርጉም ባሻገር በተለይም የኢንዱስትሪ ልማትን ለማነቃቃት የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የቀይ ባህር ቀጣና የኃያላን የጦር ሰፈር በመሆኑ የራስ ወደብ ባለቤት መሆን መቻል ለሉዓላዊነት ማስከበርም ጉልህ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።

የብዝኃ-ወደብ ባለቤት በመሆን ሎጂስቲክስን የማቀላጠፍ ጥረቱ ይቀጥላል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የኢኮኖሚ ዞኖችን ማጠናከርና መሠረተ-ልማት ግንባታዎችን በማሳለጥ ተቋሙ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ይወጣል ብለዋል።

የባህር በር ስምምነቱ የተቋሙን ተልዕኮ የተሳካ ለማድረግ ተጨማሪ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች ለስኬቱ የላቀ ተሳትፎና ትብብር እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በኮርፖሬሽኑ የስትራቴጂክ አማካሪ ኪያ ተካልኝ በበኩላቸው፤ 80 በመቶ የዓለም ኢኮኖሚ በባህር እንደሚንቀሳቀስ ገልጸው፤ ወደብ ከሀገራት ቁልፍ መሠረተ-ልማት መካከል እንደሆነ ተናግረዋል።


 

ለኢንዱስትሪ ልማት ከሚያስፈልጉ መሠረተ-ልማቶች ወደብ አንዱ መሆኑን በመግለጽም፤ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ቁልፍ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

በወጪና ገቢ ንግድ ተወዳዳሪ ለመሆን፣ ጥሬ ዕቃን ለተጠቃሚው ተደራሽ ለማድረግ ያለውን ዓይተኛ ሚና ጠቅሰው፤ ለወደብ አቅራቢያ ለሚገነቡ የኢኮኖሚ ዞኖችም ትልቅ ዕድል እንደሚያመጣ ነው የገለጹት።

በተለይም የድሬደዋ እና በቀጣይ የሚገነባውን የአይሻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስፋት በቀጣናው ለአምራች ዘርፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም