ዩኒቨርሲቲው የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበትን 50ኛ ዓመት በማስመልከት "የሉሲ ዓመት" የተሰኘና ዓመቱን ሙሉ የሚቆይ መርሃ ግብር ማካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበትን 50ኛ ዓመት በማስመልከት "የሉሲ ዓመት" የተሰኘና ዓመቱን ሙሉ የሚቆይ መርሃ ግብር ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ጥር 08/2016(ኢዜአ)፦ የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር መገኛ የምርምር ተቋም የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበትን 50ኛ ዓመት በማስመልከት "የሉሲ ዓመት" የተሰኘና ዓመቱን ሙሉ የሚቆይ መርሃ ግብር ማካሄድ ጀመረ ፡፡
ሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ አካል የተገኘችበትን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ ከተለያዩ አገራት የመጡ 28 ጎብኚዎች ብሔራዊ ሙዚየምን ጎብኝተዋል።
በጉኝቱ ሉሲን ከ50 አመት በፊት ያገኟት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሀንሰንን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የመጡ ጎብኚዎች ተገኝተዋል።
በአሜሪካ የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ኢንስቲትዩት ኦፍ ሂዩማን ኦሪጅን ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዮሃንስ ሃይለስላሴ ጉብኝቱ የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበትን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሜሪካ የሚገኘው የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር መገኛ የምርምር ተቋም በዘርፉ የተለያዩ ጥናትና ምርምርን በማካሄድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ የሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ አካልን ጨምሮ ሌሎች የሰው ልጆች ቅሪተ አካልን ያገኙ ተመራማሪዎች የሚገኙበት መሆኑንም አንስተዋል።
ዛሬ በብሔራዊ ሙዝዬም በጉብኝቱ የተሳተፉት አካላት በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸውና ለቅርሶች ደህንነት የተለያዩ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸውንም አክለዋል።
ይህ የጉብኝት መርሃ ግብር የሉሲ(ድንቅነሽ) ቅሪተ አካል የተገኘበት የ50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ማስጀመሪያ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ የሚቆይ መርሃ ግብር ማካሄድ መጀመሩን አብራርተዋል።
በመርሃ ግብሩም ሲምፖዚዬም፣ ፎቶ ኤግዚቢሽንና ሌሎች ዝግጅቶችን እንደሚያካትት ጠቁመዋል፡፡
ይህም የኢትዮጵያን የቱሪዝም አቅም ለማስተዋወቅና ምቹ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም ጎብኚዎቹ ሌሎች ቅሪተ አካል የሚገኙባቸው የአገሪቱ አካባቢዎችን ጨምሮ ታሪካዊና ተፈጥራዊ መስህቦችን እንደሚጎበኙም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል ክርስቲና ማይክል በጉብኝታቸው ኢትዮጵያ ቀደምት የታሪክና የቅርስ ባለቤት ሀገር መሆኗን መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ጉብኝት እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት፡፡
ሌላው የጉብኝቱ ተሳታፊ ኤንዲ ራይሰን ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ጠቁመው በቆይታቸው ወደ ተለያዩ ስፍራዎች በማቅናት ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል ።
በእስካሁኑ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ብዙነገሮችን እንዳዩ በቀጣይም የላሊበላን ቅርስ ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።