የጥምቀት እና የከተራ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ መላው የፀጥታ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ ገብተዋል- የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት እና የከተራ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ መላው የፀጥታ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ ገብተዋል- የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል
አዲስ አበባ፤ ጥር 08/2016(ኢዜአ)፦ የጥምቀት እና የከተራ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ መላው የፀጥታ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
የ2016 ዓ/ም የከተራና ጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር እቅድ አውጥቶ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡
ባለድርሻ አካላትና የከተማችን ነዋሪዎች የተለመደ ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስ የተመዘገበው የጥምቀት እና የከተራ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ መላው የፀጥታ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የጥምቀት በዓል ከከተራ ዕለት ጀምሮ ባሉ ተከታታይ ቀናት በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች የሚከበር ኃይማኖታዊ በዓል ሲሆን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ሐይሉ በዓላቱ ያለ አንዳች የፀጥታ ስጋት እንዲከበሩ ሊከናወኑ በሚገባቸው ተግባራት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡
ውይይቱን የመሩትና መመሪያ የሰጡት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፤ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የፀጥታ አካሉን ትኩረት ለማዛባትና የበአሉን አከባበር ድባብ ለማደፍረስ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ያላቸው መረጃዎችን እያሰራጩ መሆኑን ተናግረው የሀገር ውስጥም ሆኑ ሌሎች የሽብር ቡድኖች አለን ለማለት ያላቸውን አቅም በመጠቀም ጉዳት ለማድረስ ወደ ኋላ እንደማይሉ አስገንዝበዋል፡፡
ይሁን እንጂ የፀጥታ አካሉ ዋና ግብ በህግ የበላይነት ሰላምና ፀጥታን በማረገገጥ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ማስቻል በመሆኑ ሁሉም አመራርና አባል ይህን ተገንዝቦ ኃላፊነቱን እንደ ከዚህ ቀደሙ በብቃት ሊወጣ እንደሚገባ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው ህዝባዊ ኃይሉ ከፀጥታ አካሉ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ መመሪያ መሠጠቱን ጠቁመው በዓሉ በሰላም እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል ከማህበረሰቡ ፣ ከሃይማኖት አባቶች እና የበአሉ ጉዳይ ከሚመለከታቸው አደረጃጀቶች ጋር መድረክ ተዘጋጅቶ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የበዓሉ በሰላም መከበር ለሀገር ገፅታ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ስለሆነ በየእርከኑ የሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተግባሩን በቅርበት እየተከታተሉ ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን ወ/ሮ ሊዲያ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በዓሉ ካለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር የከተማ አስተዳደሩ ለፀጥታ አካሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
በ2016 ዓ/ም ህዝብ በስፋት ወደ መስክ በመውጣት ያከበራቸው ሀይማኖታዊ በዓላት እና ሌሎች ልዩ ልዩ ኩነቶች በሰላም መከበራቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አስታውሰው በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ማድረግ የተቻለው የፀጥታ አካላት ተናበው በመስራታቸው እና ሰላም ወዳድ ዜጎች የድርሻቸውን በመወጣታቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በሳለፍነው ሳምንት በተዘጋጁ የህዝብ መድረኮች ፖሊስ በህገ-ወጦች ላይ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ህዝቡ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነሩ ተናግረው ህብረተሰቡ በአሉን ያለስጋት እንዲያከብር የፀጥታ አካላት በቴክኖሎጂ ታግዘው ወደ ተግባር መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በበዓሉ አከባበርም ሆነ በማንኛውም ወቅት ብሄርን ከብሄር፣ ሀይማኖትን ከሀይማኖት፣ የሚያጋጩ ጭፈራዎች ፣ አልባሳቶች ፣ ፅሁፎች እና በአጠቃላይ ግጭት ቀስቃሽ ተግባራትን የማይታገስ መሆኑን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ሃይሉ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪን ተቀብለው በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለተኛ ትውልድ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የጥምቀት በዓል መከበሩ ለበዓሉ ድምቀትም ሆነ የሀገርን ገፅታ በመልካም ለማስጠራትና የተዛቡ አስተያየቶችን ለማረም የሚኖረው ሚና በቀላሉ የማይታይ በመሆኑ መላው የፀጥታ አካላት ትስስራችንን እና የመረጃ ልውውጣችንን ይበልጥ በማጠናከር የህዝብን ሰላም የማስጠበቅ ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል የሚሉ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የሀገር መከለከላያ ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ፣ የሸገር ከተማ አስተዳር ፖሊስ፣ የሠላምና ፀጥታ እንዲሁም የሌሎች የፀጥታ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡