የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ጤና ሚኒስቴር

ድሬዳዋ፤ ጥር 8/2016(ኢዜአ)፦በአገር አቀፍ ደረጃ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት በመቀነስ የምዕተ ዓመቱን ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር  ደረጀ ዱጉማ ተናገሩ።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህን የተናገሩት ዛሬ በድሬደዋ ሳብያን ጠቅላላ ሆስፒታል ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡትን የፅኑ ህሙማን ጨቅላ ህፃናት ህክምናና የፊዚዮ ቴራፒ ማዕከላትን መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።


 

በዚሁ ወቅት ሚኒስትር ደኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደተናገሩት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስና የተቀመጠውን የምዕተ ዓመቱን የጤና ግብ ለማሳካት በተከናወኑ ስራዎች  አበረታች ለውጥ ተመዝግቧል።

ነገር ግን የጨቅላ ህፃናትን ሞት በመቀነስ ረገድ  መሻሻል ቢኖርም በተፈለገው ልክ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የተጀመረውን የተቀናጀ  እንቅስቃሴ በማጠናከር የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን ነው የገለፁት።

በድሬደዋ ሳብያን ጠቅላላ ሆስፒታል የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የተገነባው ዘመናዊ የህክምና ከፍል በምሳሌነት የሚጠቀስና ይህንኑ ተግባር በማስፋት የሚፈለገውን ግብ  ለማሳካት ይሰራል ብለዋል።

" የሳብያን ጠቅላላ ሆስፒታል  ለህብረተሰቡ ወቅቱን የጠበቀ ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠትና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት እየሰራ የሚገኘው አበረታች ስራም ፍሬያማ እንዲሆን፤ ሆስፒታሉን ለህሙማን ምቹ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው አስተዳደሩ ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት  ጤናማና አምራች ትውልድ የማፍራቱ ግብ እንዲሳካ እየተረባረበ ይገኛል ብለዋል።

ድሬደዋ የምስራቅ አገሪቷ ክፍል የነፃ ንግድ ቀጠናና የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል በመሆኗ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ዘመናዊ የጤና አገልግሎቶችና የጤና ማዕከላትን ተደራሽ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል ።

ዛሬ ተገንብቶ ወደ ስራ የገባው የጨቅላ ህፃናት ዘመናዊ የህክምና ማዕከል በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ አገልግሎት መስጠት የሚያስችልና ፈር ቀዳጅ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ ናቸው።

ዶክተር ፅጌረዳ አክለው፤  ማዕከሉ በፅኑ ህሙማን ጨቅላ ህፃናት ላይ ይደርስ የነበረን ችግር  በመፍታት ጤናማ ትውልድ የማፍራቱን ግብ ለማሳካት ያስችላል።

ማዕከሉ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ የህክምና ግብዓቶች ይበልጥ መሟላት ላይ ጤና ሚኒስቴር የተለመደውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

የሳብያን ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስፈጻሚ ሲስተር መስከረም አሰፋ በበኩላቸው አስተዳደሩ በመደበው 8 ሚሊዮን 757 ሺህ ብር የተገነቡት የጨቅላ ህፃናት ማዕከልና የፊዝዮ ቴራፒ ግንባታ መጪውን ጤናማ ትውልድ ለማስቀጠልና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችሉ ገልጸዋል ።

ሆስፒታሉ  ከቅደመ ዕርግዝና እስከ ድህረ ወሊድ ያሉትን ሂደቶችና አገልግሎቶች ምቹና ተስማሚ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዲቻል በትኩረት እንደሚሠራም አውስተዋል ።

ዛሬ የተመረቀውና ወደ አገልግሎት የገባው የጨቅላ ህፃናት ህክምና ማዕከል ዘመናዊ የህክምና ክፍሎችና የህክምና መሣሪያዎች የተሟላለት መሆኑም ታውቋል።

በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የተመራው የአመራር አባላት ቡድን በሳብያን ጠቅላላ ሆስፒታል የፅኑ ህሙማን ጨቅላ ህፃናት ህክምና መርቀው ስራ ካስጀመሩ በኋላ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና የህክምና ሆስፒታልን ጎብኝተዋል።

 

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተማም አወል እንዲሁም የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሁሴን መሐመድ ሆስፒታሉ አሁን ያለበትን ደረጃ አስመልክተው ገለፃና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም