የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢያዊ ፀጋዎችን መሠረት ያደረገ ገበያ ተኮር የሰው ሀይል ስልጠና እያስፋፋ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢያዊ ፀጋዎችን መሠረት ያደረገ ገበያ ተኮር የሰው ሀይል ስልጠና እያስፋፋ መሆኑን ገለጸ
ሶዶ፣ ጥር 8 / 2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢያዊ ፀጋዎችን መሠረት ያደረገ ገበያ ተኮር የሰው ሀይል ስልጠና እያስፋፋ መሆኑን የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው አጋማሽ አፈፃፀም ግምገማና የአመራር አቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ነው።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ብቃት ያለው፣ ተነሳሽነት የተላበሰና ለሥራ ፈጠራ የተዘጋጀ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ ነው።
ይህም የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማፋጠን እገዛ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።
የክልሉን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከላት ለማድረግና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ማስፋፊያና የቴክኖሎጂ ማፍለቂያዎች እንዲሆኑ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።
በተለያዩ የሙያ መስኮች መደበኛና የአጫጭር ጊዜ ሥልጠናዎች በመስጠት የሰው ሃይል በማቅረብ ሰራተኛና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን በማፍራት ለኢኮኖሚያዊ እድገት ድርሻውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተለይም አሁን ላይ በሙያና ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ገበያ ተኮር ስልጠናን ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን ኃላፊው አስረድተዋል።
በክልሉ የሚገኙ አምስት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በመካኒክ፣ በግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በጨርቃጨርቅ ስፌትና አልባሳት እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም መስኮች በተግባር የተደገፈ የክህሎት ስልጠና መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት አካባቢያዊ ፀጋዎችን በመጠቀም ሀብት ለመፍጠር የጀመሩት እንቅስቃሴ ሊጎለብት ይገባል ብለዋል።
አካባቢን በመቃኘት በገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በተግባር የተደገፈ ስልጠና ወሳኝ መሆኑን ያስረዱት ዶክተር አበባየሁ፣የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሀገራዊ ተልዕኮውን ለማሳካት በተገቢው የሰው ኃይል ማደራጀት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የክልሉ መንግሥት በቀጣይም ተቋሙን በሥልጠና መሣሪያዎች፣ ማሽነሪዎች እንዲሁም የስልጠና ቦታዎች በማመቻቸት እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።