ጥምቀትና የባህል አልባሳት ገበያ - ኢዜአ አማርኛ
ጥምቀትና የባህል አልባሳት ገበያ
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2016(ኢዜአ)፦ ጥምቀትና የባህል አልባሳት ገበያ
የጥምቀት በዓል በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ የተጠመቀበትን ዕለት በማሰብ የሚከበር ደማቅ በዓል ነው።
በመላ ኢትዮጵያ በሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ተነስተው፣ በየጥምቀተ ባሕሩ የሚያድሩ በመሆኑ ፣ ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብ በመፍጠርም ቱሪስቶችን እየሳበ ይገኛል፡፡
የበዓሉ ታዳሚ ምዕመናን፣ የካህናትና የዲያቆናት አለባበስ ፍፁም በሚማርክ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁል ጊዜ አዲስ ነው።
''ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ'' እንደሚባለው በየደረጃው ያለ የህብረተሰብ ክፍል የክት ልብስ ለብሶ አምሮና ደምቆ ከተራን ለማክበር በተለያዩ የታቦታት ማደሪያ መታደማቸውም እንዲሁ የተለመደ ነው።
የበዓሉ ታዳሚያን ከበዓሉ አስቀድሞ ሸማቾች አጊጠውና ደምቀው ለመታየት ወደ ባህል አልባሳት መሸጫ መደብሮች ያመራሉ።
ኢዜአ በአዲስ አበባ የሽሮሜዳ የባህል አልባሳት ገበያ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ሸማቾችና ነጋዴዎች የባህል አልባሳት ገበያው ሞቅ እያለ መሆኑን ተናግረዋል።
ተጠቃሚዎች እንዳሉት የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ባህላዊ እሴቱን ሳይለቅ የተዘጋጁ የባህል አልባሳትን በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ዘመኑን በሚመጥንና በሁሉም የእድሜ ደረጃ ተዘጋጅተው የሚሸጡ የባህል አልባሳት ወጣቱ በሀገሩ የባህል ልብሶች እንዲኮራና እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አብራርተዋል፡፡
በገበያ ማዕከሉ ያገኘናቸው ነጋዴዎች በበኩላቸው፤ የጥምቀት በዓል የባህል አልባሳት ለመሸመት ወደ ሽሮ ሜዳ ለሚሄዱ ሸማቾች የባህል አልባሳት ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት ህብረተሰቡ ለባህል አልባሳት የነበረው ትኩረት እየተቀየረ መሆኑንና በአገሩ ምርት የመኩራት ልምዱ ሁሌም መሆን እንዳለበት ገልፀዋል።