ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ትስስርን አጠናክራ ትቀጥላለች-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ትስስርን አጠናክራ ትቀጥላለች-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ትስስርን አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት አገሮች ጉዳዮች ዳሬክተር ዘሪሁን አበበ ለኢዜአ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና መነሻውና ማጠንጠኛው የጎረቤት ሀገራት ናቸው።
ፖሊሲው ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላምን በማስፈንና ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር ወደ አፍሪካ ማስፋትን ማዕከል ያደረገ ነው።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ትስስር ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
በቀጣናው ትብብር እንዲጎለብት ካደረገቻቸው እንቅስቃሴዎች መካከል የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) በልማት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንዲመሰረት ያደረገችውን አስተዋጽኦ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በተናጠልም ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ትስስርን ለማጠናከር በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ ሃይል፣ በንግድ ያከናወነቻቸው በርካታ ተግባራትን ዘርዝረዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ ተግባራዊ በማድረግ በሱዳን፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ሰላም ማስፈን ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች።
ባለፉት 30 አመታት በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ ያደረገችው ጥረት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሽብርተኝነትን በመዋጋት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2006 ጀምሮ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረጓን በማስታወስ፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መጠናከርና ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ትስስርን ለመፍጠር የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል በአጽእኖት አንስተዋል።
በአፍሪካ እንዲሁም በቀጣናው ያለውን ሃብት በጋራ ተጠቃሚነትና ሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ተመስርቶ ማልማት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ትስስርን ማምጣት ትልቅ የትኩረት አቅጣጫዋ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል።
ለዚህም ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ በመሆኑ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ መሰረተ ልማትን ማስፋፋትና የንግድ ትስስርን ማጠናከር በትኩረት እየሰራችባቸው ከሚገኙ ጉዳዮች ውስጥ ዘርዝረዋል።
ኢትዮጵያ በሰላም፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርታ የምታነሳቸውን የመልማት ጥያቄዎችንም መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ቀንድ በተፈጥሮ ሃብት፣ በባህልና ቋንቋ የተሳሰረ በመሆኑ ይህን እድል ወደ ጠንካራ ትስስር በመቀየር ቀጠናውን ተጽእኖ ፈጣሪ ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡