ቀጥታ፡

የኃይል ማመንጫ ግድቦች በደለል ሳይሞሉ ለረዥም ዘመናት እንዲያገለግሉ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2016(ኢዜአ)፦ የኃይል ማመንጫ ግድቦች በደለል ሳይሞሉ ለረዥም ዘመናት እንዲያገለግሉ የተፋሰስ ልማትና የአረንጓዴ ማልበስ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የውሃ ግድቦችን እንደ ዋነኛ የኃይል ልማት አማራጭ በመውሰድ ከራሷ አልፋ የአካባቢውን አገራትም ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራች መሆኑ ይታወቃል።

ከቆቃ እስከ ኮይሻ፣ ተከዜ፣ መልካ ዋከና፣ የጊቤ እና የሕዳሴ ግድቦች የታዳሽ ኃይል ምንጮች በዘርፉ ልማት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

የኃይል ማመንጫ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉና በቂ ውሃ እንዲይዙም ካልተደረገ በሚፈለገውና በሚጠበቀው ልክ አገልግሎት መስጠት አያስችላቸውም።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ፤ የተቀናጀ የተፋሰስና የአረንጓዴ ልማት ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

የተፈጥሮ ኃብትን በመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከልና አካባቢን ከማልማት ባለፈ በተለይም የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከደለል ሙላት ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአፈር መሸርሸር ሳቢያ በተለይም የኃይል ማመንጫ ግድቦች የደለል መሞላት ችግር ስለሚያጋጥማቸው በዘላቂነት የመከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የኃይል ማመንጫ ግድቦች በደለል ሳይሞሉ ለረዥም ዘመናት እንዲያገለግሉ ግድቦቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች የተፋሰስ ልማትና የአረንጓዴ ማልበስ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

ለተፋሰስ ልማት ሥራዎች በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት  ጋር በመቀናጀት በጂኦግራፊያዊ የመረጃ ሥርዓቶች (ጂ አይ ኤስ) አካባቢዎችን ቀደም ብሎ የመለየት ሥራ መከናወኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

በመቀጠልም የተፋሰስ ልማትና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከኃይል ጠቀሜታ ባለፈ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እየሰራች መሆኑ ይታወቃል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተፈጠሩት ከ70 በላይ ደሴቶች ጥሩ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች መሆን የሚችሉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም