የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለስራም ሆነ ለትምህርት ወደ የትኛውም ሀገር ሰዎችን የመላክ ተግባር ላይ እንዳልተሰማራ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለስራም ሆነ ለትምህርት ወደ የትኛውም ሀገር ሰዎችን የመላክ ተግባር ላይ እንዳልተሰማራ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለስራም ሆነ ለትምህርት ወደ የትኛውም ሀገር ሰዎችን የመላክ ተግባር ላይ የተሰማራ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳሰበ።
ዕቃ ለተላከላቸው ደንበኞቹ መድረሱንና ወደ ድርጅቱ በመምጣት አስፈላጊ ሂደቶች እንዲያስጀምሩ ከማሳወቅ ውጪ ምንም አይነት ቅድመ ክፍያ በስልክ የማይጠይቅ መሆኑንም አየር መንገዱ አስታውቋል።
ከዚህ በፊት አጭበርባሪዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ የእቃ ጭነት አገልግሎት(ካርጎ) በኩል ለተለያዩ ግለሰቦች ዕቃ እንደተላከላቸው አስመስሎ በመደወልና ሐሰተኛ የእቃ ጭነት መለያ ቁጥር Air Waybill (AWB) በመጠቀም ዕቃውን ለመቀበል የሚከፈል በሚል ገንዘብ እንደሚጠይቁ አስታውሷል።
ስራ ፈላጊዎችንም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመቀጠር ለምዝገባና ለተለያዩ ወጪዎች በሚል ገንዘብ በማስከፈል የማታለል ተግባር ላይ መሰማራታቸውንና ማሕበረሰቡ ይህንን አውቆ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቡንም አየር መንገዱ አንስቷል።
በቅርቡም አጭበርባሪዎች የካናዳ መንግስት የስራና የትምህርት እድል እንዳወጣና ተቋሙ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሰው እንደወከለ መመዝገብ ለሚፈልጉ ሁሉ ክፍያ የሚፈፅሙበት የባንክ አካውንትም አንዳሳወቀ በማስመሰል ደብዳቤ በማዘጋጀት ሰዎችን የማታለል ተግባር ላይ መሰማራታቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል።
ለስራ ቅጥር ምንም ዓይነት ቅድመ ክፍያ የማይጠይቅ እና ከማንኛውም ዓይነት ኤጀንት ጋር አብሮ የማይሰራ መሆኑን አየር መንገዱ ገልጿል።
በተጨማሪም ለስራም ሆነ ለትምህርት ወደ የትኛውም ሀገር ሰዎችን የመላክ ተግባር ላይ እንዳልተሰማራም ነው በማህበራዊ ትስስር ገጹ የገለጸው።
እቃ ለተላከላቸው ደንበኞቹም ዕቃቸው መድረሱንና ወደ ድርጅቱ በመምጣት አስፈላጊ ሂደቶችን እንዲያስጀምሩ ከማሳወቅ ውጪ ምንም ዓይነት ቅድመ ክፍያ እንዲከፍሉ በስልክ የማይጠይቅ መሆኑን አስታውቋል።
ማሕበረሰቡም ይህንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክቱን አስተላልፏል።