አቶ ደመቀ መኮንን ከአለም ኢኮኖሚ ፎረም ኘሬዝደንት ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አቶ ደመቀ መኮንን ከአለም ኢኮኖሚ ፎረም ኘሬዝደንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2016(ኢዜአ)፦ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአለም ኢኮኖሚ ፎረም ኘሬዝደንት ጋር ውይይት አካሄደዋል።
ለ54ኛ ጊዜ በዳቮስ ስዊዘርላንድ በመካሄድ ላይ ባለው የአለም ኢኮኖሚ ፎረም እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ደመቀ መኮንን ከፎረሙ ኘሬዝደንት ቦርግ ብሬንድ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ላይ አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የምጣኔ ሃብት እምርታዎች ገለፃ ያደረጉ ሲሆን እድገትን ለማስቀጠል እና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ መንግስት መሰረታዊ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ቁልፍ የሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማስፋፋት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ በራስ አቅም የገነባችውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በማሳያነት አንስተዋል።
የአገልግሎት ዘርፉን ተደራሽ ለማድረግ፣ የፋይናንስ ተቋማትን ለማሻሻልና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ድርሻ ለማሳደግ መንግስት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ኘሬዝደንት ቦርግ ብሬንድ ፥ ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚካሄደው የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ጉባኤ ላይ ለአመታት ሳታቋርጥ ለቀጠለችው ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይ ፎረሙ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የቅርብ ግንኙነት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚፈልግም ኘሬዝደንቱ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።