ቤጂንግ ያለ አሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ የፖሊስ ፓትሮሎችን አስተዋወቀች

564

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2016(ኢዜአ)፦ የቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ ያለ አሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ የፖሊስ ፓትሮል ተሽከርካሪዎችን በማስተዋወቅ የእንቅስቃሴ ሙከራ አካሄደች።

ተሽከርካሪዎቹ ለአካባቢ ቅኝት፣ ለህዝባዊ በአላት ደህንነት እንዲሁም ለድንገተኛ አደጋ የመከላከል ስራዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ በመረጃው ተመልክቷል።

ቤጂንግ እ.አ.አ በ2020 በስማርት ሲቲ ማዕቀፍ ስር 160 ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት ያለው አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱበት አካባቢ የገነባች ሲሆን የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆኑ አሽከርካሪ አልባ የፖሊስ ፓትሮሎችን አስተዋውቃለች።

ተሽከርካሪዎቹ ደረጃ አራት ያለ አሽከርካሪ የሚያንቀሳቀስ መኪና ቴክኖሎጂ እንደተገጠመላቸው እና በየ30 ሰከንዱ ራሱን የሚያድስ ባትሪ በዚህም 100 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም እንዳላቸው ተነግሯል።

በተጨማሪም ተሽከርካሪዎቹ በ120 ሜትር የአካባቢ ስፋት ውስጥ የሚካሄዱ ነገሮችን የመለየት ብቃት እና የመንገድ ደህንነት ግብረ መልስ የሚሰጥ ቴክኖሎጂ እንደተገጠመላቸው ነው የተመላከተው።

በቤጂንግ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች ልምምድ ቦታ የተዋወቁት 15 የፖሊስ ፓትሮሎች ሲሆኑ ከፖሊስ መኮንኖች ጋር በመሆን የአደጋ ጊዜ ልምምድ ማካሄዳቸውንም የዘገበው ሲጂቲኤን ነው።

በአሽከርካሪ አልባ ፓትሮሎቹ የተካሄዱት ሙከራዎች በአደባባይ ዝግጅቶች ደህንነትን ማረጋገጥ፣ ህዝባዊ ማስጠንቀቂያዎችን መስጠት እና የአደጋ ጊዜ ተልዕኮዎችን መለየት መሆናቸው ተመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት በቤጂንግ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች ልምምድ ቦታ ላይ 28 አምራች ኩባንያዎች መሰማራታቸው እና 800 ተሽከርካሪዎች ደግሞ በሙከራ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም