ቀጥታ፡

አቶ ደመቀ መኮንን በአለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2016(ኢዜአ)፦ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው።

የአለም ኢኮኖሚ ፎረም በዳቮስ ስዊዘርላንድ መካሄድ ጀምሯል።

ለ54ኛጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የዘንድሮው ጉባኤ ጭብጥ " መተማመንን ዳግም መገንባት" የሚል ሲሆን፥ ቁልፍ በሆኑ አለም አቀፍ የልማት ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ አየር ንብረት ለውጥና ወቅታዊ የደህንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

አቶ ደመቀ በጉባኤው ላይ እያደረጉት ካለው ተሳትፎ ጎን ለጎን ከሃገራት መሪዎች እና ከተቋማት ሃላፊዎች ጋርም ውይይት አድርገዋል።



 

ከታንዛኒያ ምክትል ኘሬዝደንት ፊሊኘ ምፓንጎ ጋር በነበራቸው ውይይትም አቶ ደመቀ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ያብራረሩ ሲሆን የኘሮጀክቱ አጠቃላይ ስራ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልፀውላቸዋል።

የታንዛኒያ ምክትል ኘሬዝደንት ፊሊኘ ምፓንጎ በበኩላቸው፥ በአባይ ውሃ ሃብት ላይ ፍትሃዊ አጠቃቀም በተፋሰሱ ሃገሮች መካከል እንዲሰፍን ታንዛኒያ የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች በውይይት እንዲቋጩ ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል ።

የሁለቱ ሃገራት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባን በቅርቡ ለማካሄድ ተስማምተዋል።

አቶ ደመቀ ሌላውን ውይይት ያደረጉት ከአለም አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዳረን ታንግ ጋር ሲሆን ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላት ትብብር ሊጠናከር በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗንም ተናግረው ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አቶ ደመቀ ያቀረቡላቸው ጥሪም ተቀብለዋል።

ዋና ዳይሬክተር ዳረን ታንግ የአለም አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም