ቀጥታ፡

በአፋር ክልል ህገ ወጥ ደላሎችን በመከላከል የግብይት ሂደቱን ወደ ህጋዊ ስርዓት ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ሰመራ ፤ ጥር 07/2016 (ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ህገ ወጥ ደላሎችን በመከላከል የግብይት ሂደቱን ወደ ህጋዊ ስርዓት ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕስ መስተዳደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎልቤ ሲሌ ሰብሳቢነት የተለያዮ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት ኃላፊው አቶ ጎልቤ ሲሌ እንደገለጹት በክልሉ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተለያየ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

በክልሉ ህገ ወጥ ደላሎችን በመከላከል ግብይቱን ወደ ህጋዊ ስርዓት ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። 

ለዚህም እንዲረዳ የወጣቶች አደረጃጀትን በመጠቀም በቀጥታ አምራቹ ምርቱን በሰመራና ሎጊያ ከተሞች እንዲያቀርብ ይደረጋል ብለዋል።

ይህ ሲሆን ህብረተሰቡ በቀጥታ ከተዘጋጁ ማዕከላት ምርቶችን በመሸመት የገቢያ ክፍተቱን መሙላት ያስችላል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ከንግድ ምክር ቤት ጋር በመቀናጀት ህገ ወጥነትን የመከላከል ስራ የሚከናወን ሲሆን ግብረ ኃይል በማቋቋም ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ ንግድ፣ ገበያ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አደን ሒንኬብ በበኩላቸው የምርት አቅርቦቱ በተሳለጠ መልኩ እንዲከናወን ክትትልና ቁጥጥር ይጠናከራል ሲሉም ገልጸዋል።

ህገ ወጥ ደላሎችን በመከላከል ሻጭና ገዥውን ቀጥታ በማገናኘት የግብይት ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የሠመራ ሎጊያ ከተማ እና የዱብቲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የዞን አስተዳዳሪና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም