ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት በሶስት ክልሎች ከ900 መቶ በላይ ነጋዴዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ 

አዲስ አበባ፤ ጥር 07/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት በሶስት ክልሎች ከ900 መቶ በላይ ነጋዴዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል፡፡

ምክር ቤቱ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ የሚያደርገው ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (ጂአይዜድ) ጋር በመተባበር መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

የምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ አቶ ውቤ መንግስቱ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ፕሮጀክቱ ለቀጣይ 14 ወራት በኦሮሚያ፣ አማራና ሲዳማ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው፤ በዚህም 930 ነጋዴዎችን ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከምርት እስከ ግብይት ያለውን ሰንሰለት ውጤታማ ለማድረግ ዓላማ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡


 

በተለይም የሽንኩርት፣ አቮካዶ እና አኩሪ አተር ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም  የገበያ ሰንሰለት ስርዓትንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል የገበያ ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የምርትና ምርታማነትን፣ የገበያ ዝግጅትና አቅርቦትን በተመለከተ የአቻ ለአቻ የልምድ ልውውጥ፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናና ድጋፍ በማድረግ ነጋዴዎችን ለማብቃት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

የጀርመን መንግስት ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚውል 553 ሺህ 192 ዩሮ ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የምርት አቅርቦት ሰንሰለትን በማሻሻል ገበያ ለማረጋጋት ሚናው የጎላ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎንም የገበያ ሰንሰልትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ምርምሮችንና ውይይቶችን በማድረግ  ለፖሊሲ አውጪዎች  ሀሳብ የማቅረብ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የፕሮጀክቱ ውጤታማነት ከተረጋገጠ በኃላ  በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም