የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ በአግባቡ በማወቅና በመረዳት የትውልዱ ተሳትፎ እንዲጠናከር መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ በአግባቡ በማወቅና በመረዳት የትውልዱ ተሳትፎ እንዲጠናከር መስራት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥር 07/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ በአግባቡ በማወቅና በመረዳት የትውልዱ ተሳትፎ እንዲጠናከር ቀጣይነት ያለው ስራ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ ከቀናት በፊት በሳይንስ ሙዚየም ለእይታ ክፍት መደረጉ ይታወቃል።
በአውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የሚያስረዱ የተለያዩ መገለጫዎች ተዘጋጅተዋል።
በመስኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሎም በአፍሪካ የተጫወተችው ሚና፣ የገጠሟት ፈተናዎችና ያለፈችባቸው መንገዶች ተሰንደው ለዕይታ ቀርበዋል።
ኢትዮጵያ ለአህጉር አቀፍ ድርጅት ምስረታ፣ ለጥቁር ህዝቦች ትግል ያበረከተችው አስተዋጽኦና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጀግኖች በየፈርጁ ተዘጋጅቶ ለጎብኝዎች ክፍት ሆኗል።
የተለያዩ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ የሙያ ማህበራትና ሌሎችም አውደ ርእዩን በመጎብኘት ላይ ሲሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሙያዎችም ገለጻና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በአውደ ርእዩ ላይ ሲጎበኙ ያገኘናቸው አቶ በቀለ ገዳ፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ታሪክ ተሰንዶ ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉን አድንቀዋል።
የኢትዮጵያን የረጀም ጊዜ የካበተ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በትውልድ ቅብብሎሽ ሁሉም በቅጡ እንዲያውቀው ለማድረግ እንዲህ አይነት ሁነቶች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመው አውደ ርእዩን በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ በአግባቡ በማወቅና በመረዳት የትውልዱ ተሳትፎ እንዲጠናከር ቀጣይነት ያለው ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ መሀመድ አህመድ ቆጴ፤ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ለሀገራቸው የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን ለማወቅ አውደ ርዕዩ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት የተከናወኑ ተግባራትን በመረዳት የአሁኑ ትውልድም የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት መሰል ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
በጉብኝት ላይ ያገኘናቸው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አየለ ለገሰ፤ ከአውደ ርእዩ በዲፕሎማሲው መስክ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለመረዳት የሚያስችል ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዶክተር መለስ ዓለም፤ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይን እስካሁን በርካቶች እየጎበኙትና የተለያዩ ግብአቶችንም እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ ቀናት ሌሎችም እንዲጎበኙ ጥሪ አስተላልፈዋል።