ተባባሪ አካላት በየአካባቢያቸው ህዝብን በማንቃት ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ሊተጉ ይገባል- ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ተባባሪ አካላት በየአካባቢያቸው ህዝብን በማንቃት ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ሊተጉ ይገባል- ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ሀዋሳ ፤ ጥር 7/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተባባሪ አካላት በየአካባቢያቸው ህዝብን በማንቃት ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ውጤታማነት ሊተጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አሳሰቡ።
ኮሚሽኑ አጀንዳ ማሰባሰብና ምክክር ላይ የሚሳተፉ የማህበረሰብ አባላትን ለመመልመል ለሚያግዙ ተባባሪ አካላት ያዘጋጀው የስልጠና መድረክ ዛሬ በሻሸመኔ ከተማ ተጀምሯል።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንዳሉት የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ተዋናይ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።
በመሆኑም ተባባሪ አካላት በየአካባቢያቸው ህዝብን በማንቃት ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ውጤታማነት ሊተጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ የሀገራዊ ምክክሩ ተባባሪ አካላት ስልጠናን ከወረዳ ጀምሮ በሰፊው እያካሄደ መሆኑን ጠቁመው ይህም በሀገራዊ ምክክር ፅንሰ ሀሳብና ዓላማ ላይ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለያዩ ክልሎች ሲሰጥ የቆየው የተባባሪ አካላት ስልጠና በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ተጠናክሮ መቀጠሉን አመላክተዋል።
በየደረጃው በሚካሄደው በዚሁ ስልጠናው ላይ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እንደሚሳተፉ ጠቅሰው ሰልጣኞቹ ለምክክሩ የሚሆኑ አጀንዳዎችን ነቅሰው በማውጣትና በክልል ደረጃ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር ለኮሚሽኑ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
አጀንዳ የሚሰጡ ሰዎች ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ ኮሚሽኑ በአስቸኳይ አጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ እንደሚገባ ነው ፕሮፌሰር መስፍን ያስረዱት።
ኮሚሽኑ አጀንዳዎችን በየክልሉ በሚሰበስብበት ወቅት ጎን ለጎን ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ እንደሚያደርግ ጠቅሰው ይህም ስራውን ለማሳለጥ ያስችላል ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ አሳታፊና አካታች እንዲሁም ስኬታማ እንዲሆን የክልል መንግስታት፣ በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች፣ የጸጥታና የደህንነት አካላት እንዲሁም የኃይማኖት ተቋማት ባለድርሻ መሆናቸውን በመግለጽ ከነዚህ አካላት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ በበኩላቸው ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግስት እንዲኖር ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
ለሀገራዊ ምክከሩ መሳለጥ የተባባሪ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው እነዚህ አካላት በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ይዘው ተሳትፏቸውን ለማጠናከር እንዲችሉ በየደረጃው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ክላስተር ላይ ለሶስት ቀናት በተዘጋጀው ስልጠና ላይ ከቦረና ዞኖች፣ ምእራብና ምስራቅ ጉጂ እንዲሁም ከባሌ ዞኖች ስር የሚገኙ 68 ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከባሌ ዞን ሮቤ ከተማ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ ፓስተር ይልማ አብዲ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ የገጠሟትን የተወሳሰቡ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
ምክክሩ የሀገሪቱን ችግሮችና ቁርሾዎች በዘላቂነት ለመፍታትና ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከምስራቅ ቦረና ዞን የመጡት ሌላኛው ተሳታፊ አቶ ከድር ዋቀዮ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ውጤታማ ሆኖ ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት እንዲችል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚደረገው ምክክር ስር የሰደዱ አንገብጋቢ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያስችል ጠቅሰው እሳቸውም የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።