ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በገበታ ለሀገርና ሌሎች ፕሮጀክቶች የተገነቡ የመስህብ ስፍራዎችን ለውጭው ዓለም እያስተዋወቅን ነው-አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2016(ኢዜአ)፦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት በተለያዩ አካባቢዎች የለሙ አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችን በውጭው ዓለም የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አምባሳደሮች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅዷ ካስቀመጠቻቸው አምስት የኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጫ ምሶሶዎች አንደኛው ቱሪዝም ነው።

ዘርፉን ለማጠናከርም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎች ለምተዋል።

ለአብነትም በአዲስ አበባ የሚገኙት የአንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ እና እንጦጦ ፓርክ ለጎብኝዎች ክፍት ሆነው ገቢ እያስገኙ ነው።

በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም ጨበራ ጩርጩራ፣ ሃላላ ኬላ፣ ኮይሻ እና ወንጭ የአካባቢውን ባህልና ስርዓተ ምህዳር በጠበቀና በዘመናዊ መልኩ  ተገንብተው ስራ ጀምረዋል።

በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክትም በርካታ የመስህብ ስፍራዎችን ለመገንባት ወደ ስራ ተገብቷል።

በፈረንሳይና በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደሮች በተለያዩ አካባቢዎች እየለሙ የሚገኙ እነዚህ መስህቦችን የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ እንዳሉት፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጭነት አዲስ የለሙና ነባር የመስህብ ስፍራዎች ለውጭው ዓለም የማስተዋወቂያ መርሐግብር በመቅረፅ እየተሰራ ነው።

ለዚህም ኤምባሲው ከኢትዮጵያ አየር መንገድና አስጎብኝ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የውጭ ዜጎች ስለኢትዮጵያና የቱሪዝም ሀብትቿ እንዲያውቁ  እያደረገ ነው ብለዋል።

እንደ አምባሳደር ማህሌት ገለጻ ፓሪስ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መቀመጫ እንደመሆኗ ኢትዮጵያ  ያስመዘገበቻቸውን ቅርሶች የማስተዋወቅ ስራም በቅርበት እየተከናወነ ነው።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር በበኩላቸው፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እየለሙ ያሉ የመስህብ ሀብቶች የዕይታ ለውጥ ያመጡና ለሀገር ተጨማሪ እሴት የፈጠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኤምባሲው የቱሪስት መዳረሻዎችን በተለያዩ ሁነቶች በማስተዋወቅ ኢትዮጵያ ውብ የሆኑ በርካታ የሚጎበኙ ሀብቶች እንዳላት ግንዛቤ መፈጠሩን  ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎም በርካቶች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ፍላጎት እያሳዩ ነው ብለዋል።

አምባሳደሮቹ አክለውም ኢትዮጵያ ከፈረንሳይና ፓኪስታን ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ትብብር መስኮች የበለጠ ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደር ጀማል ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ሰፊ አማራጭና ምቹ ከባቢ እንዳላት ግንዛቤ መፈጠሩን ተከትሎ በርካታ የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።

አምባሳደር ማህሌት በበኩላቸው የኢትዮጵያንና የፈረንሳይን የንግድ ትስስር የበለጠ ለማጠናከርና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን ጥሪ የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው አምባሳደሮቹ የገለጹት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም