ቀጥታ፡

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል-የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ጥር 07/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በመጪዎቹ  ወራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምክር ቤት ላለፉት አራት ወራት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ እቅድ አፈጻጸም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ገምግሟል።


 

በመድረኩም ባለድርሻ ተቋማት ሲያከናውኑት የቆዩት ቅንጅታዊ አሰራር ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ 

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም በዚሁ ወቅት፤ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት ላለፉት አራት ወራት ሰፊ ስራዎችን ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል።

ስራዎቹም በዋናነት በሀገሪቷ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በመድረኩም በባለፉት አራት ወራት የተከናወኑ ስራዎች አፈጻጸም ላይ ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ በዚህም ባለድርሻ ተቋማት በእቅዳቸው መሰረት የተሻለ ስራ ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመጪው የበልግ ጊዜም የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቷ አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ ለመቋቋም በምክር ቤቱ በኩል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ካለፈው ከሀምሌ ወር ጀምሮ በመንግስት በኩል 11 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በአጋር ድርጅቶች 4 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ሰብዓዊ ድጋፍ  በችግር ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።

በመጪዎቹ የጥር፣የካቲትና መጋቢት ወራትም 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ይህም በገንዘብ ሲተመን ወደ 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ከምግብ እህሎች ጋር ተያይዞም በሚቀጥሉት 3 ወራት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሰራጭ ሲሆን፤ ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው በኮሚሽኑ በኩል እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

ቀሪው በአጋር ድርጅቶች በኩል የሚቀርብ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም